Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያን ከተደቀነባት የውስጥና የውጭ ፈተና ለመታደግ በተግባር ዘብ ቆመናል – የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 10 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል መንግስትና ህዝብ ኢትዮጵያን ከተደቀነባት የውስጥና የውጭ ፈተና ለመታደግ እዘምታለሁ፤የትም፤መችም፤ በምንም የሚለውን ሀገራዊ መሪ ቃል በተጨባጭ በመተግበር ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ።

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ሁኔታ ላይ ዛሬ በሰጠው መግለጫ አሸባሪዎቹ የሕወሐት/ጁንታና ኦነግ-ሸኔ ግንባር ፈጥረው የወጠኑትን ሀገርን የማፍረስና እልቂትን የመፍጠር አጀንዳ በማምከን ሀጋራዊ ሉአላዊነትና ነፃነት ያላንዳች መንገራገጭ ለማስቀጠል ዘብ ቆመዋል ብሏል።

የክልሉ መንግስት በመግለጫው እንዳስታወቀው የሉአላዊነታችን ጋሻና መከታ ለሆነው ለጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን ደጀን ለመሆን ከገጠር እስከ ከተማ፣ ከወጣት እስከ አዛውንት፣ አንድም ሳይቀር በኢትዮጵያዊነት የማሸነፍ ወኔ የተቃኘው የክልላችን ሕዝብ የተባበረ ክንድ በሚታይም ሆነ በስውር ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያሰፈሰፉ የውስጥና የውጭ ሃይሎችን አስደንግጧል፡፡

ሕዝቡ በገንዘብና በቁሳቁስ ጀግናውን የመከላከያ ሠራዊታችንን ከመደገፍ አልፎ በተለይ ወጣቱ በአካል ሠራዊቱን በመቀላቀል እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ያሳየው ጀግንነትና ቁርጠኝነት ታሪክ የማይረሳው ነው ብሏል።

ለጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን ጠንካራ ደጀን ለመሆን የተጀመረው እንቅስቃሴ በሁለንተናዊ መልኩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጧል፡፡

ሀገርን ለመታደግ በተቀመጠው መርሀ ግብር መሰረት ጀግናው የክልላችን ህዝብ በሁሉም የትግል አውድ መሰማራቱን የጠቀሰው የክልሉ መንግስት መግለጫ፤ ከትንሹ ቁሳዊ አስተዋፅኦ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በሚችለው ሁሉ ከጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን ጎን ተሰልፏልም ነው ያለው፡፡

በዚህ ፈታኝ ምዕራፍ ኢትዮጵያን ለማዳን ሁሉ-አቀፍ ርብርብ በምናደርግበት በዚህ ወቅት ሁኔታዎችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የማይገባቸውን ሀብት ለማካበት የሚጥሩ ጥቂት ስግብግብ ነጋዴዎች መኖራቸው እንደተደረሰባቸው አመልክቶ፣ ለህዝብና ለሀገር ደንታ የሌላቸው ያለቸውን እነዚህን ግለሰቦች በኢትዮጵያ ላይ ይፋዊ ጦርነት ከከፈተው ከአሸባሪው የሕወሐት ጁንታ ለይተን አናያቸውም ሲል አስጠንቅቋል፡፡

በህገ ወጥ መንገድ ሀብት ለማካበት ብቻ በዚህ የሀገርና ህዝብ ክህደት ተግባር ውስጥ የተሳተፉ ነጋዴዎች እጃቸውን በፍጥነት እንዲሰበሰቡ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አሳስቧል፡፡

በአመለካከትና በድርጊት የባንዳነትና ተላላኪነት ተግባር ለመወጣት የንግዱን ስርዓት ለማዛባት በዘመቱ ቡድኖች ላይ መንግስት አስተማሪና የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑንም አስገንዝቧል፡፡

ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን መሰረት ያደረገ የዋጋ ንረት እንደተጠበቀ ሆኖ በጥቂት ግለሰቦች ራስ ወዳድነት የሚፈጠረው የዋጋ ጭማሪ ሕዝብን ባሳተፈ መልኩ እንዲጋለጥ የክልሉ መንግስት ጥሪ አቅርቧል፡፡

በዚህ ሂዳት ውስጥ የተሰጠውን ሃላፊነት በመዘንጋት የህዝቡን መብትና ጥቅም በሚጎዳ ተግባር ውስጥ ሲሳተፍ በተገኘ የመንግስት የስራ ሃላፊም ሆነ ባለሙያ ላይ መንግስት የማያወላዳ እርምጃ እንደሚወስድ መግለጫው አሳስቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.