Fana: At a Speed of Life!

በተደራጀና በተናበበ ህዝባዊ ንቅናቄ አሁን ያጋጠመንን ችግር እንመክታለን – አቶ ተስፋዬ ቤልጂጌ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 11 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በተደራጀና በተናበበ ህዝባዊ ንቅናቄ አሁን ያጋጠመንን ችግር እንመክታለን ፤ቀልብሰን ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ እናወጣለን ሲሉ አቶ ተስፋዬ ቤልጂጌ ተናገሩ ፡፡
ከመላው የአገሪቱ አካባቢዎች የተወጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ በሚንስትር ማዕረግ የምርጫና የዲሞክራሲ ግንባታ ማዕከል ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ዛዲግ አብርሃ በሰሜን በኩል የተከፈተው ጦርነት ከኢትዮጵያዊያን ፍላጎት ውጭ የስርዓት ለውጥ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ጠቅሰው የኢኮኖሚ አሻጥር እንዲፈጠር በማድረግ ህዝቡ በኑሮ ውድነቱ ተማሮ መንግስት ላይ ለማነሳሳት እየሰሩ ስለመሆናቸው ተናግረዋል፡፡
እንደ አገር የመጣውን ሁለንተናዊ ለውጥ ለመቀልበስና ያለፈውን ጨቋኝ ስርዓት ለመመለስም አሸባሪው የህወሓት ቡድን የሞት ሽረት እያደረገ በመሆኑ ጊዜ ሳናባክን የህልውና ዘመቻውን በአጭር ጊዜ ቋጭተን ወደ መደበኛ የልማት ስራዎች ልንመለስ ይገባል ብለዋል፡፡
በሚንስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ቤልጂጌ በበኩላቸው በተደራጀና በተናበበ ህዝባዊ ንቅናቄ አሁን ያጋጠመንን ችግር እንመክታለን፤ቀልብሰን ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ እናወጣለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አሸባሪው የህወሓት ቡድን ዓላማ ኢትዮጵያ ውስጥ ደካማ መንግስት እንዲፈጠር በማድረግ የምዕራባዊያን ተላላኪ ማድረግና ኢትዮጵያን ማፍረስ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ኡመር ኢድሪስ የውጭ ሃይሎች የራሳችንን ጉዳይ በራሳችን እንድንፈታ በውስጥ ጉዳዮቻችን ላይ ጣልቃ እንድትገቡ አንፈቅድም ሲሉ አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል በመወከል በውይይቱ የተገኙት ፕሮፌሰር እያሱ በአማራና በአፋር ክልሎች ላይ የደረሰው ዘግናኝ ጭፍጨፋ ቤተ ክርስቲያኗን በእጅጉ ያሳዘነ መሆኑን ጠቅሰው መንግስት ህግ ለማስከበር እያደረገ ያለውን ዘመቻ እንደግፋለን ብለዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ወክለው የተገኙት መላከ ህይወት አባ ገብረ ጊዮርጊስ ደግሞ በሐይማኖት ጥላ ስር ተጠልለው ለአሸባሪው የህወሓት ቡድን የሚሰሩ ሰዎች መኖራቸውን ጠቅሰው መንግስት ፍተሻ ማድረግ አለበት ሲሉ ማሳሰባቸውን ከብልፅግና ፓርቲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.