Fana: At a Speed of Life!

ህወሓት ሂሳቡን የሚያወራርደው ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር እንጂ ከአማራ ህዝብ ጋር ብቻ አይደለም-አቶ ሙስጠፌ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሃመድ በክልሉ ከተለያዩ ቢሮዎች ከተውጣጡ አመራሮች አና ሰራተኞች ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች፣ በመንግሥት ሰራተኞች ኑሮ መሻሻል እንዲሁም አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ መክረዋል፡፡

ሰራተኛች በፍጆታ እቃዎች እና በኑሮ ውድነት፣ ከመስሪያ ቤቶች ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮች፣ በሰራተኞች ምደባና ደመወዝ ጋር ተያይዞ የተለያዩ ጥያቄዎች እና አስተያየቶችን አንስተዋል።

በክልሉ የነበሩ አመራሮች ከአሸባሪው ህወሓት የሚቀበሉትን ተልዕኮዎች ለማስፈጸም ብቻ ሰራተኛውን ለስብሰባ ይጠራ እንደነበርም ነው የገለጹት፡፡

የመንግሥት ሰራተኞቹ አሸባሪውን የህወሓት ጁንታ በሚነዛው ፕሮፓጋንዳና መሠረተ ቢስ መረጃዎች እንደማይበገሩም ተናግረዋል።

የሶማሌ ክልል ሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልቃድር አብዲ÷ የመንግሥት ሰራተኞች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች መፍትሔ እያገኙ መሆኑን በመጥቀስ÷ ሁሉም ባለው የትምህርት ደረጃ መሰረት እየተመደበ ነው ብለዋል፡፡

አቶ ሙስጠፌ ሙሃመድ በበኩላቸው÷ ከለውጡ በኋላ በሶማሌ ክልል ሁለንተናዊ ለውጥ እንደመጣና በክልሉ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሰላም እየኖረ መሆኑን አውስተዋል፡፡

በሶማሌ ክልል ማንም ሰው በብሄሩና በአመለካከቱ ችግር እንደማይደርስበትና ለህግ ተገዥ ሆኖ ሃሳቡን በነፃነት የመግለጽ መብት እንዳለውም ጠቅሰዋል፡፡

ህወሓት በፕሮፓጋንዳ ሀገር የማፍረስ አቅም የለውም ያሉት አቶ ሙስጠፌ÷ አወራርዳለሁ የሚለው ሂሳብ ከአማራ ጋር ብቻ ሳይሆን ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ከአሸባሪ ህወሓት ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች የክልሉ መንግሥት ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድም አረጋግጠዋል፡፡

የመንግሥት ሰራተኞች ለህዝቡ ተገቢ አገልግሎት እንዲሰጡና ከወገንተኝነትና ከፍርሃት በጸዳ መልኩ ስራቸውን እንዲሰሩ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከሶማሌ መገናኛ ብዙሃን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.