Fana: At a Speed of Life!

ተላላኪው ሽኔ በኦሮሞ ስም የመታገል ሞራል ሊኖረው አይችልም – የምዕራብ ጉጂ ዞን ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 12፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሸባሪው ህውሓት ተላላኪ የሆነው ኦነግ ሽኔ በኦሮሞ ስም የመታገል ምንም አይነት ሞራል ሊኖረው አይችልም ሲሉ የምዕራብ ጉጂ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ።

ኦነግ ሸኔ ከህወሓት ጋር ግንባር ፈጥሮ ሀገር ለማፍረስ መነሳቱ ከጥፋት ውጭ አማራጭ ሃሳብ እንደሌለው የሚያሳይ መሆኑን ነዋሪዎቹ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ከመከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላት ጎን በመቆም አሸባሪ ቡድኖችን እንደሚታገሉ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

በዞኑ የአባያ ወረዳ ነዋሪ አቶ ኢትዮጵያ ኮዬ እንዳሉት÷ “ተላላኪው ኦነግ ሸኔ ንጽሃንን የሚገድል፣ ሴቶችን አስገድዶ የሚደፍርና ንብረት የሚዘርፍ ተራ የወንጀል ቡድን ነው” ብለዋል።

ኦነግ ሸኔ በሚፈጽማቸው ተግባራት ከህወሓት የሚለየው ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።

“አሳዳጅና ተሳዳጅ የነበሩት ሁለቱ አሸባሪ የጥፋት ቡድኖች ሀገር ለማፍረስ የሚችሉት ቀድመው እኛን ማፍረስ ሲችሉ ብቻ ነው” ሲሉም ገልጸዋል።

“ከአሸባሪው ህወሓት ጋር ግንባር የፈጠረው ተላላኪው ሽኔ በኦሮሞ ስም የመታገል ሀቅና ሞራል ሊኖረው አይችልም” ያሉት ደግሞ የገላና ወረዳ ነዋሪ አቶ ብዙነህ ካያሞ ናቸው።

በኦሮሞ ስም የተደራጀው አሸባሪው ኦነግ ሸኔ ለኦሮሞ እናቶችና ህጻናት ሰላም ከመስጠት ይልቅ ሲጨፈጭፍና ሲያርድ መቆየቱን ተናግረዋል።

“ከመንግስትና ከመከላከያ ጎን ቆመን ጠላታችን የሆነውን ቡድኑን ለመታገል ቁርጠኞች ነን” ያሉት አቶ ብዙነህ÷ “ብሄር ብሄረሰቦች በጋራ ቡድኑን አሶግደን እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በአንድነት እንኖራለን” ብለዋል።

በዞኑ የጓንጓ ከተማ ነዋሪ አቶ ሽፈራው ኡዴ በበኩላቸው÷ ኦነግ ሸኔ ባለፉት 27 አመታት ሀገር ሲያምስና ኦሮሞን ሲጨፈጭፍ ከነበረው ህወሀት ጋር ግንባር መፍጠሩ ደካማ የጥፋት ቡድን መሆኑን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

“ይህ ቡድን ህዝባችንን ሲጨፈጭፍና ሲያርድ የኖረ ነው፤ እኛ ደግሞ በአንድነት ቆመንይህን ጠላታችንን ከላያችን ላይ አሽቀንጥረን ጥለን ልማታችንን እናስቀጥላለን፤ አሁን ላይ ቡድኑን ከአካባቢያችን እያስለቀቅን ነው” ብለዋል።

“ሀገርን ለከዳ ባንዳ የምንሰጠው ምንም አይነት እድል ሊኖር አይገባም” በማለት ነው አቶ ሽፈራው አስተያየታቸውን ያጠቃለሉት ።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.