በኦሮሚያ በ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር የሚካሄዱ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች የኮንትራት ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሚያ ክልል የውኃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ግንባታቸው በ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር የሚካሄድ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች የኮንትራት ውል ስምምነት ከስራ ተቋራጮች እና አማካሪዎች ጋር ተፈራረመ።
የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶቹ በ13 ዞኖች ውስጥ የሚካሄዱ ሲሆን፥ በዚህም 12 የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች እና 53 የጉድጓድ ውሃ ቁፋሮ ፕሮጀክቶች እንደሚካሄዱም ነው የተገለፀው።
ከዚህ በተጨማሪም በዛሬው እለት የተፈረመው ስምምነት የአራት ከተሞች የዲዛይን ጥናትን የሚያካትት መሆኑም ከኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የኦሮሚያ ክልል የውኃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ በስምምነቱ ላይ ፕሮጀክቱ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚካሄድ ሲሆን፥ ከ434 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል።
በኦሮሚያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው፥ በክልሉ እስካሁን የንጹህ መጠጥ ውሃ 65 በመቶ ብቻ መሆኑን በማንሳት 35 በመቶው እስካሁን ተደራሽ አልሆነም ነው ያሉት።
በዛሬው እለት የተፈረመው ስምምነትም ከዚህ ቀደም የንጹህ የመጠጥ ውኃ ተደራሽ ላልሆነባቸው ቅድሚያ የሚሰጥ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
እንደ ሀገር የተጀመረው ለውጥ ከግብ የሚደርሰው ሁሉም የበኩሉን ሲወጣ ነው ያሉት ዶክተር ግርማ፥ በዛሬው እለት ስምምነት የተፈራረሙ የስራ ተቋራጮችም ለህዝብ ወገንተኝነት ቅድሚያ በመስጠት በተለያዩ ምክንያቶች ሳይዘናጉ ስራቸውን በማጠናቀቅ ህዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።