Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ግንባር ቀደም አርሶና አርብቶ አደሮችን በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለማሰማራት ዝግጅት ተጠናቋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል 5 ሺህ ግንባር ቀደም አርሶ እና አርብቶ አደሮችን ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በንግድ እና አገልግሎት ዘርፍ ለማሰማራት የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁ ተገለፀ።

በሀገሪቱ ግንባር ቀደም አርሶ እና አርብቶ አደሮችን  በመለየት በተለያዩ ሽልማቶች ማበረታታት ከተጀመረ ዓመታት አልፏል።

በዚህ ውስጥ በምርት፤በሃብት እና በቁጠባ የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ፤ ከራሳቸው ባለፈ በሀገር ደረጃ በሚመዘን አሻራቸው እየተለዩ በሜዳሊያ፣ ዋንጫ እና ሌሎች ማበረታቻዎች እና ሽልማቶች እየተሰጣቸው ለሌሎችም አርዓያ ይሆኑ ዘንድ የታሰበው ፕሮግራም ዛሬም ቀጥሏል።

ይሁን እንጂ  በግንባር ቀደሞቹ የተሰበሰበው ጥሪት ትርጉም ባለው መልኩ ለሌሎች በሚተርፍ፣ ስራን ፈጥሮ ለሌሎች አያሌ ወጣቶች ሀብት ማፍሪያነት በሚውል መልኩ እንዳልተሰራበት  ይነገራል።

ለምሳሌ በኦሮሚያ ክልል ግንባር ቀደም አርሶ እና አርብቶ አደር ተብለዉ ከብዙዎች የክልሉ አርሶ አደሮች የላቀ ዉጤት በማስመዝገብ  ለዚህ ሽልማት የበቁት ቁጥራቸው 1 ሚሊየን መድረሱን የክልሉ የገጠር ክላስተር ቢሮ መረጃ ያመላክታል።

ይህን ሃብት  በተቀናጀ መልኩ ደምብ እና ስርዓት ተበጅቶለት ሌሎችን ቀጥረው ወደሚያሰሩበት አሰራረ ማሳደግ ባለመቻሉ  ክልሉ ቁጥራቸዉ ከፍ ባሉት ስራ አጦች እንዲሞላ መንገድን የከፈተ መሆኑም ይነገራል።

በኦሮሚያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ ከፋና ብሮድካሰቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ ካሁን በኋላ ይህ መሰል አሰራር አይቀጥልም ብለዋል።

ለአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ሜዳሊያ ከመሸለም በዘለለ ቀጣይነት ያለው ነገር ማድረግ ይገባል በማለት።

የክልሉን ህብረተሰብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ እንደ አንድ አቅጣጫ የተቀመጠው ግንባር ቀደም አርሶ አደር ተብለው የተለዩትን ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በንግድ እና አገልግሎት ዘርፎች  ላይ ለማሳተፍ ይሰራልም ብለዋል።

በዘንድሮ ዓመት ብቻ 5 ሺህ አርሶ አደሮችን ወደዚሁ ለማስገባት ቅድመ ዝግጅቴን አጠናቅቄያለሁ የሚለው ክልሉ፥ ሂደቱ የተሳለጠ እና ከአሰራር ችግር የፀዳ እንዲሆን የክልሉን ኢንቨስትመንት ደምብ የማሻሻል ስራ መከናወኑንም አስታውቋል።

አርሶ እና አርብቶ አደሮቹም ቢሆኑ ወደዚህ ስራ ሲሰማሩ በተለያዩ ህጋዊ መስመሮች ማለፍ ሊጠበቅባቸው እንደሚችል በመጥቀስ   ለዚህም በግብርና ቢሮ የአግሪ ቢዝነስ ዳይሬክቶሬት ተቋቁሟል ብለዋል ዶክተር ግርማ።

ግንባር ቀደም አርሶና አርብቶ አደሮችን ኢንቨስተመንት፣ በንግድና አገልግሎት የማሰማራት እቅዱ 50 ሺህ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል እንደሚፈጥር ከወዲሁ ተገምቷል።

ለስኬቱም የተለያዩ ሴክተሮች የ50 ቀን እቅድ አውጥተው እየሰሩበት መሆኑ  ነው የተገለጸው።

እንደ ዶክተር ግርማ ገለፃ፥ እቅዱ  የአርሶ አደሩን እና አርብቶ አደሩን ህይወት ከማሻሻሉ ባለፈ 50 ሺህ የሚሆኑ  ወጣቶችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

በአፈወርቅ አለሙ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.