Fana: At a Speed of Life!

በኦነግ ስም ከወያኔ ጋር የተገባው የሴረኞች አፍራሽ ስምምነት ኦነግን አይመለከትም

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ስም ከወያኔ/ትህነግ ጋር የተገባው የሴረኞች አፍራሽ ስምምነት ኦነግን አይመለከትም።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር  ያወጣው የአቋም መግለጫ  እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ከቅርብ ቀናት በፊት በኦሮሞ ነጻነት ግንባር/የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ስም ከወያኔ/ትህነግ ጋር የትግል አጋርነት መመስርቱን የሚገልጽ መግለጫ መለፈፉ ይታወቃል።

ሆኖም ግን ይህ መግለጫ የሴረኞችና ሃገር አፍራሾች እንጂ የኦነግ ውሳኔና አቋም አለመሆኑን ወዳጅም ሆነ ዘመድ እንዲያውቀው አበክረን ለማሳሰብ እንወዳለን።

የኦነግ በነጻነት ትግሉ ውስጥ ድርጅታዊ ነጻነቱን ጠብቆ በራስ ላይ በመመርኮዝ ሲታገል የነበረና የማንም ጥገኛና ተቀጥያ ያልሆነ ድርጅት በመሆኑ የሚታወቅ፡  በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ክብርና ተወዳጅነት ያለው የፖለቲካ ድርጅት ነው።

እንዲሁም ወታደራዊ ክንፉ የነበረው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት የኦሮሞን ህዝብ ከበሬታ ያገኘ ሰራዊት ነበር። ዛሬ በነዚህ  ስም በመጠቀም ወያኔዎች በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል እያካሄደ ካለው ጦርነት ጋር ለማበር የተለፈፈው አጋርነት በምንም መልኩ ኦነግን የማይመለከትና ከኦነግ ህግ፡ ስርዓትና ስትራተጂ ውጪ ከመሆኑም ባሻገር የድርጅቱን ታሪክ የሚያጎድፍና የሚያጠለሽ የመሰሪዎች ተግባር  ነው ብለን እናምናለን።

የደርግ መንግስት ከወደቀበት ከ1983 ዓም ጀምሮ በትህነግ የበላይነት ሲመራ የነበረው ወያኔ መራሹ የኢህአደግ መንግስት የስራ አስፈጻሚውን መዋቅር በመቆጣጠር ህግ በማውጣት፡ የመከላከያ ሰራዊትን፡ ደህንነትን፡ የፍትህ አካላትን በሙሉ በበላይነት ከመቆጣጠር አልፎ የሃገሪቷን ኢኮኖሚ በአንድ ፓርቲ አስተዳደር ስር በማስገባት የሃገር ሃብት ሲዘርፍ፡ ተወዳዳሪ የማይገኝለት የሰብዓዊ መብት ረገጣዎችንና ጭቆናዎችን ሲፈጽም እንደነበር ማንም የሚገነዘበው የቅርብ ግዜ ትውስታ ነው። ይህን አስከፊ ስርዓት ለማስወገድ የፖለቲካ ሃይሎችና ሰፊው ህዝብ ከፍተኛ መስዋዕትነት የጠየቀ መራራ ትግል አካሂደዋል። በተለይም በኦሮሞ ቄሮና ቀሬ የተቀጣጠለው ከኦሮሚያ አልፎ ሃገሪቷን ያዳረሰው ሰፊ የጸረ ጭቆና ትግል የወያኔን ስርዓት ከስሩ ነቅንቆ ማዳካሙ ሁሉም የሚገነዘበው እውነታ ነው።

ይህ ህዝባዊ ትግል በወያኔ/ኢህአዴግ ውስጥም ለውጥ ፈላጊዎች እንዲፈጠሩ በማስቻሉ በታህሳስ 2010 ለ17 ቀናት በተካሄደው ስብሰባ ራሱን በመገምገም ለመለወጥ መወሰኑ ይታወሳል።

ህዝብና በኢህአዴግ ውስጥ የተፈጠሩት የለውጥ ፈላጊዎች ተዳምረው በፈጠሩት ጫና ዶክተር ዓቢይ አህመድ በኢህአዴግ አመራርነት እንዲመረጡ አስችሏል። የኦሮሞ ህዝብ ይህን የታየውን ለውጥ መቀበሉም አይታበልም።

ከለውጡ ጋር ተያይዞ ሲወሰዱ የነበሩ እርምጃዎች ማለትም የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት የአስቸኳይ ግዜ አዋጅን ማንሳት በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩትን ድርጅቶች ጨምሮ ሁሉም ድርጅቶች ወደ ሃገር ቤት እንዲመለሱ መደረጉ ከጎረቤት ሃገር ኤርትራ ጋር ሰላም ማስፈን መቻሉና ሌሎች የመሳሰሉ እርምጃዎች አበረታችና ተስፋ ሰጪዎች እንደነበሩ ይታወቃል።

ይህ እንዳለ ሆኖ የታሰበው ለውጥ እንደታሰበው ወደፊት ሊራመድ አልቻለም ማለት ይቻኣላል። ላለው ዕንቅፋትና ለለውጡ ችግር ውስጥ መግባት ዋነኛው ምክንያት ኢህአዴግ ውስጥ የታየው ልዩነትና በተናጠል በኢህአዴግ ድርጅት አባሎች መካከል የተከሰተው ልዩነት ነው ብለን እናምናለን።

በወያኔና በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል የነበረው ፉክክር የስልጣን መሆኑም በግልጽ ይታይ ነበር። በመሆኑም ወያኔ ራሱን ከኢህአዴግ አርቆ መቀሌ በመመሸግ ወታደራዊ አቅሙን ማጎልበትን ተያያዘው። ይህ እርምጃ በመቀጠሉ ለሃገሪቷ  የሁለት ሃገር መልክ ሰጣት።  የኦነግ ይህን ክስተት በጥንቃቄ ሲመለከተው ቆይቷል። በመካከላቸው የተከሰተው ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታም ሃሳብ ሲያቀርብ ነበር።

ይሁን እንጂ የተከሰተው አለመግባባት በለውጥ ፈላጊዎችና ለውጡን በሚቃወሙ ሃይሎች መካከል መሆኑ ከኦነግ የተሰወረ አልነበረም።

በሌላ በኩል ተስፋ ለተጣለበት ለውጥ ደንቃራ የሆነውና ጥርጣሬ ያጫረው የብሄር ብሄረ ሰቦችና ህዝቦችን መብትና         የዜግነትን መብት በማጣጣም አብሮ ከመራመድ በጭቆና ስር ነበርን የሚሉ ህዝቦች በትግላቸው ያገኙትንና በህገ መንግስቱ የተረጋገጠውን  በፌደራላዊ ስርዓት የመተዳደርና የብዛሃነት መብት ተወግዶ የድሮ ስርዓት እንዲመለስ በሚድያዎች የሚስተጋባውና የሚወደሰው አመለካከት ያለውን የፖለቲካ ችግር ይበልጥ ውስብስብ አድርጎት ለብዙዎች የስጋት ምንጭ መሆኑ አያጠራጥርም።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ይህን አመለካከት ሲቃወም ነበር። አሁንም ይቃወማል።ይሁን እንጂ በብዙሃን ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ይህ ኋላ ቀር አስተሳሰብ በሚዲያ ላይ ስለተስተጋባ በትጥቅ እንታገለዋለን የሚል አቋም የለውም። ይህን ያረጀና ሚዛን የማይደፋ አመለካከት ለመታገልም ደቦ ፍለጋ ወደ ሌላ ተቀናቃኝ አልሄደም። ይህን ኋላ ቀር አስተሳሰብ ለመታገል ከሌላ ይበልጥ ኋላ ቀር አስተሳሰብ አራማጅ ሃይልን አይወዳጅም፡ አያግዝም።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከመንግስት ጋር ተደራድሮ በመስማማት ወደ ሃገር ቤት ሲመለስ በትህነግ በኩል ተቃውሞ እንደነበር ይገነዘባል። የኦነግ ከወያኔም ጋር ይሁን ከሌላ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ጋር በድብቅ ያደረገው ስምምነት የለም። ከወያኔ ጋር ምንም አይነት ውይይትና ግንኙነት አልነበረውም። ኦነግ እውነተኛ ፈደራላዊ ስርዓት ሰላምና ዴሞክራሲ ለማስገኘት በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ለመታገል ወደ ሃገር ቤት የተመለሰ ድርጅት እንጂ የትጥቅ ትግል ለማካሄድ አልተመለሰም።

ለስላም ካለው ፍላጎት በመነሳት በተናጠል ተኩስ በማቆም ከመንግስት ጋር በጠብመንጃ መፈላለግ ቆሞ በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋትን እውን ማድረግ፡ ከኔ ሌላ የሚለውን አስተሳሰብ በማስቀረትና በድርጅቶች መካከል ያለውን  የጠላትነት አመለካከት በማስወገድ በወንድማማችነት የሃገርን ጥቅም በማስቀደም መስራት አስፈላጊና ወሳኝ መሆኑን በማመን ነው/\። ሃገርንና ኦሮሚያን ከሚመሩት ፓርቲዎች እንዲሁም የኦሮሚያ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሌሎች በሃገሪቷ ከሚገኙ ፓርቲዎች ጋር እንዴት አብሮ መስራት እንደሚቻል በመወሰን ለትብብር ሲሰራ ቆይቷል። በተለይም በወቅቱ ኦሮሚያን ሲመራ የነበረውን ፓርቲ ጨምሮ ለኦሮሞ ህዝብ መብት መከበር ከሚታገሉ ከኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የኦሮሚያንና የኦሮሞን  እንዲሁም የሃገሪቷን ጥቅም ለማስከበር አብሮ ለመስራት ወስኖ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ይታወሳል።

በመኖኑም ኦነግ ወደ ሃገር ቤት ከተመለሰ በኋላ ከተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ምክክር ሲያካሄድ እንደነበር ይታወቃል። በዚህ ውይይትና ምክክር የተሳኩ እንዳሉ ያልተሳኩም ነበሩ። ከተካሄዱት ውይይቶች ውስጥ ከጅምሩ የተደናቀፈው ከወያኔ ጋር የታሰበው ነበር።

ለዚህም ምክንያቱ በሁለቱ ድርጅቶች መካከል የነበረው መጥፎ ግንኙነት ነው።  በሁለቱ ደርጅቶች መካከል ለረዥም ግዜ ሳይፈታ የቆየ  የጦርነትና የጠላትነት ግንኙነት መሆኑን የኦነግ አመራር ሲገልጽ ቢቆይም በወያኔ በኩል ኦነግ ከጎኑ እንዲሰለፍ መሻትና ለህዝባቸውና ለአባላቶቻቸው ኦነግ ከኛ ጋር ነው በማለት ሲናገሩ እንደነበር ይታወቃል።

ከኦነግ አመራርና አባላት ውስጥ ጥቂቶች በጠብመንጃ የማምለክና ወያኔን የማሞገስ ባህሪ እየታየ መምጣቱና እንደ አመራር ግልጽ የሆነ የጋራ አቋም ባለመያዙ ህዝባችን ከመወናበዱም በተጨማሪ ቅሬታ ጥርጣሬና ሃሜት ማስከተሉ አይታበልም።

የኦነግንና የወያኔን ግንኙነት አስመልክቶ የሚወራው ምንድን ነው? በድብቅ ተስማምተው አብረው እየሰሩ ነው ወይስ አይደለም? አብረው ናቸው ከተባለ ኦነግ እንዴት ብሎ ወያኔ በኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ በተለይም በኦሮሞ ህዝብ ላይ ሲፈጽም የቆየውን ግፍ በመርሳት ያለ ምንም ምክክር አብሮ ለመስራት ተስማማ? የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎች ከህዝባችንና ከሌሎች አካላት ሲቀርቡ ተስተውሏል።

ይህም ባለፈው አመት በኦነግ ውስጥ ችግር እንዲፈጠር ካደረጉት ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ነው።  አንዳንድ የአመራር አባላት በደብቅ ከወያኔ ጋር በማበር የንብረትና የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያገኙና እንዳይታወቅባቸውም ሲክዱ እንደነበር በተለያዩ ግዜያት ሲገለጽ ቆይቷል። በድርጅቱ ውስጥ የተከሰተው ይህ አለመግባባት ጥርጣሬ ፈጥሮ በድርጅቱ መዋቅር ውስጥ ሌላ ድብቅ መዋቅር እስከመዘርጋት ደርሶ ችግር ማስከተሉ የሚካድ አይደለም።  ለዚህም ተጠያቂው ከወያኔ ጋር ወዳጅነት ፈጥሬአለሁ በማለት ላይ የሚገኘው ቡድን ነው።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኣንደ ወያኔ ካለ በኦሮሞ ህዝብና በነጻነት ትግሉ  ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ  በፕሮፓጋንዳና ወታደራዊ ዘመቻ ኦነግንና የነጻነት ትግሉን ሲዋጋ የነበረን ጨፍጫፊ ቡድን ቀርቶ ከሌላ አጋር መሆን ከሚችል ድርጅት ጋር እንኳን ስምምነት ሲያደርግ የሚተገብረውና የሚከተለው ስርዓት ያለው ድርጅት ነው። ኦነግ ከሌላ ድርጅት ጋር ትብብር ለመፍጠር ቢያንስ የድርጅቱ የበላይ አመራር ማወቅና መስማማት የግድ ይላል። በየእርከኑ ያሉ የድርጅቱን አባላትና ደጋፊውችን ማማከርን ይጠይቃል። ጥቂት ሰዎች ከወያኔ ጋር ሲያድርጉትን የነበረው  ግንኙነት ግን  የድርጅቱ  ስርዓት ያልተከተለና ያፈነገጠ ነው።

በኦነግና በወያኔ መካከል የነበረው ግንኙነት የግጭትና የጦርነት ግንኙነት መሆኑን የኦሮሞ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ዓለም የሚያውቀው እውነታ መሆኑ አያጠራጥርም።

ወያኔ ከዘመነ ደርግ ጀምሮ በግልጽም ሆነ በስውር  የኦነግን ዓላማና የኦሮሞን ብሄርተኝነት በጥቅሉ የኦሮሞን የነጻነት ትግል ቢቻለው ለማጥፋት ካልሆነም ተቀባይነት እንዳያገኝ ለማድረግ ያልፈጸመው ግፍና ያልፈነቀለው ድንጋይ አልነበረም። ለወያኔ መመሪያው ለነበረው አብዮታዊ ዲሞክራሲ ዋነኛ ጠላት የኦሮሞ ብሄርተኝነት፡ ኦነግ፡ የኦሮሞ ልሂቃን፡ የኦሮሞ ባለሃብቶች ናቸው በማለት ፈርጆ ለማጥፋት በጭካኔ የተሞላ እርምጃ ሲወስድ እንደነበር አይዘነጋም።  ወያኔ ከተመሰረተበት ዕለት ጀምሮ ኦነግ የኦሮሞን ህዝብ ለመምራት ብቃት የለውም፡ ኦሮሞም ራሱን ማስተዳደር አይችልም፡ራስን የማስተዳደር ጥያቄ ማንሳት የለበትም በማለት የኦሮሞን ትግል ሲቃወም የቆየ ድርጅት ነበር።

ወያኔ በዘመነ ደርግ ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ትብብር ለመፍጠር ጥሪ ሲያስተላልፍ በነበረበት ወቅት ኦነግን በጀሌነት በወያኔ ስር ለማሰለፍ በማሰብ እንጂ በእኩልነትና እንደ ስትራተጂያዊ አጋርነት በማሰብ ባለመሆኑ በውቅቱ የተካሄዱት ምክክሮች ፍሬ ሳያፈሩ መክነው ቀርተዋል። በ1983 ሆነ ከዚያ በኋላ በሁለቱ ድርጅቶች መካከል የነበረውን ግንኙነት ለማሻሻል በተለያዩ አካላት የተደረጉ ጥረቶችም በርካታ ነበሩ።

በ1983–1984 በቻርተር ግዜና በኋላ ሶስተኛ አካል በተገኘበት በኦነግና ትህነግ መካከል የነበረውን አለመግባባት ለመፍታት ብዙ ሙከራዎች ቢደረጉም በወያኔ እምቢ ባይነት ሳይሳካ ቀርቷል። ወያኔ በስልጣን ላይ በቆየበት 27 ዓመታት ውስጥ ተቆጥሮ የማያልቅ ግፍ በኦሮሞ ህዝብና በኦነግ ላይ ፈጽሟል።

በዘመነ ወያኔ በኦሮሞ ህዝብ ላይ የተፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት በዓይነትም ሆነ በብዛት ከወያኔ በፊት የነበሩት መንግስታት ከፈጸሙት የከፋ እንጂ ያነሰ አይደለም። ወይኔ ኦሮሞን በጅምላ በመግደል የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽመውበታል። በሃረርጌ ወተር፡ ሃማሬሳ፡ ባሌ ጋራ ጅሎ፡ ሲግሞና ጋትራ ሆራ ሃርሰዴና በሌሎች አካባቢዎች የተፈጸሙት የጅምላ ግድያዎች ለዚህ ቋሚ ማስረጃዎች ናቸው።

በኦሮሞ ህዝብና በኦነግ ላይ ባወጁት ጦርነት የኦነግ አመራር አባላት፣ የፖለቲካ መሪዎችና በሺህዎች የሚቆጠሩ ውድ የህዝብ ለጆች በጥይትና በእስር ቤት ተሰቃይተው እንዲያልቁ አድርገዋል። በተለይም በ1984 ከዚያም በኋላ በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ላይ ያደረሰው ጉዳት በኦነግ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛውና ለዘላለም የሚዘክር ነው።በተጨማሪም የከተማ ነዋሪዎችና አርሶ አደሮች ቤት በመግባት ንብረት በሃይል ዘርፈዋል። በሺህዎች የሚቆጠሩ  ከፍንፊኔና ከኦሮሚያ የታፈኑ የኦሮሞ ታጋዮች እስከዛሬ ድረስ የት እንደደረሱ አይታወቀም። በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች ከሃገራቸው ተፈናቅለው ወደ ጎረቤትና ሩቅ ሃገራት እንዲሰደዱ በማድረግ ለአስከፊው የስደተኛ ኑሮ አጋልጠዋል።በዓሳ ተበልተው የቅሩትን ቤት ይቁጠራቸው። የኦሮሞን መሬትና የተፈጥሮ ሃብት በመዝረፍ ሃብት ሲያካብቱና ሲከብሩ የተንደላቀቀ ኑሮ ሲመሩ በተቃራኒው የኦሮሞ ህዝብ ለሃብቱ ባዕድ ሆኖ በድህነት እንዲሰቃይ አድርገውታል።

የወያኔ ካድሬና ሰራዊት ምንም መሳሪያ የሌለውን የኦሮሞ ዜጋ ባለቤቱ ፊት እንዲሁም ሚስትን ባለቤቷ ፊት አውርደዋል። ወንድ ሴት ልጅ ሽማግሌ ሳይሉ ሁሉንም አዋርደዋል። የኦሮሚያን ድንበር እንዳሻቸው ወስነዋል። ጎረቤት ህዝቦች በኦሮሞ ላይ በማነሳሳት ግጭት እንዲፈጠር በማድረግ ለንጹሃን ደም መፍሰስ ምክንያት ሆነዋል። የቱላማና የሃረርጌን ኦሮሞ በመቶ ሺህዎችና በሚለዮን ከቄዬአቸውና ንብረታቸው አፈናቅለዋል።

ታዲያ ይህ እውነታ እየታየና እየታወቀ ከላይ ከተዘረዘሩትና ሌሎች ተዘርዝረው የማያልቁ የጭካኔ እርምጃዎች ተዘንግተውና ምንም ዕርቀ ሰላም ሳይደረግ እንዴት ተብሎ ነው ከኦነግ እውቅና ውጪ ከኦሮሞ ህዝብና ከሃገሪቷ ብሄር ብሄረ ሰቦች ቀንደኛ ጠላት ጋር ተወዳጀን የሚባለው።

ወያኔ በኦሮሞ ህዝብ ላይ ለፈጸመው ወንጀልና ላደረሰው ጉዳት በግልጽ የኦሮሞን ህዝብ ይቅርታ ሳይጠይቅ፡ በወያኔ አስተዳደር ክፍንፊኔና ከሌላ ቦታ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ኦሮሞዎች ተፈናቅለው አስከፊ ኑሮ እየገፉ ላሉት ምንም ካሳ ሳይከፈላቸው፡ ልጆቻቸው የተገደሉባቸውና ያለጧሪ የቀሩ ወላጆች መፍትሄ ሳያገኙ፡ ከፍተኛ የጦር ወንጀልና የሰብዓዊ መብት ረገጣ ያካሄዱ የወያኔ አመራር አባላት የሰሩት ወንጀል በገለልተኛ ወገን ተጣርቶ ለፍርድ ሳይቀርቡ፡ በ1984 የዘረፉትን የኦነግ ንብረት ሳይመልሱ፡ የኦነግን አመራር ጨምሮ የት እንደደረሱ ያልታወቁ እስረኞች ሁኔታ ሳይታወቅና ቤተሰቦቻቸው ሳያውቁና እስር ቤት በድብደባ አካላቸው የጎደለና የሞቱ እንዲሁም የስነ ልቦና ጉዳት የደረሰባቸው ካሳ ሳያገኙና በኦሮሞ ህዝብና በኦነግ ላይ ላደረሱት ከፍተኛ ጥፋት ይቅርታ ሳይጠይቁ እጃቸው በኦሮሞ ደም የጨቀየውን ወያኔን ደግፎ ኦሮሞን ወይም ሌላን ወገን ለመዋጋት መሰለፍ ምን ይባላል? ትርጉሙስ ምንድነው? በወያኔ የዘር ማጥፋት ወንጀል የተፈጸመባቸው ብሄሮች፡ ብሄር ብሄረ ሰቦችና ህዝቦችስ ምን ይላሉ? በኦነግና ኦነሰ ስም የፈሰሰው የኦሮሞ ልጆች ደም ምን ይላል? የኦሮሞ ህዝብስ ይህን ምን ይላል? ከወያኔ በማበር ወደስልጣን መመለሱስ ለኦሮሞ ምን ይፈይዳል? ወያኔ ይሻላል ብላችሁ ያለ ሃፍረት የምትናገሩትስ ኦሮሞ ራሱን ለማስተዳደር ሳይሆን በሌላ ለመተዳደር ነው የታገለው? ለህዝባቸው መብት መከበር የተቻላቸውን ያበረከቱትን የኦነግ ነባር አመራሮችንና ታጋዮችን በጠላትነት ፈርጆ ወያኔን መዛመድ ተቀባይነት አለው ብላችሁ ታምናላችሁ?  ወንድምን ጠላት በማለት ከጠላት ጋር መሰለፍ በኦሮሞ ባህል ቅቡልነት ይኖረዋል?

በመጨረሻም በኦነግ/ኦነሰ ስም ከወያኔ ጋር ትብብር ተፈጥሯል በማለት የተሰራጨው መግለጫ መሰረተ ቢስና በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ነው። እየተናፈሰ ያለው መግለጫ ጥቂት ግለሰቦች ለግልና ለቡድን ጥቅም ሲሉ ያደረጉት ሊተገበር የማይችልና በአጭሩ የሚቀጭ የጸረ ህዝቦች ሴራ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ይህ አጉል ውል የኦሮሞን ህዝብ ጥቅምና የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚጎዳ እንጂ ምንም አይፈይደውም።

በመሆኑም የኦሮሞ ህዝብ በዚህ ሴራ አይወናበድም። የኦሮሞ ህዝብ ጠላትና ወዳጁን ለይቶ ያውቃል። ፍላጎቱንም ጠንቅቆ ያውቃል። ወያኔን ይታገላል እንጂ በራሱ ላይ ለመጫን አይሻም። ይህንንም ይገነዘባል። በመሆኑም የኦሮሞ ህዝብ የኦሮሞን ህዝብና የሃገሩን ጥቅም በማስቀደም ራሱን በማደራጀት ከፊቱ የተጋረጠውን አንጋፋ ጠላቱን እንዲጋፈጠው ጥሪያችንን እናቀርብለታለን።

 

ድል ለሰፊው ህዝብ!

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር

ነሃሴ 12, 2013

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.