Fana: At a Speed of Life!

የክምር ድንጋዩ አባ ረፍረፍ ጀብዱ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 14 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አቶ ጌጤ መኳንንት ወልዴ ይባላሉ በደቡብ ጎንደር ዞን ጉና በጌምድር ወረዳ የክምር ድንጋይ ነዋሪ ሲሆኑ በሆቴል ንግድ ስራ ይተዳደራሉ፡፡

ሉዓላዊነታችንን እየደፈረ ያለውን ጁንታ አቅም ምን እንደሚመስል ገምተዋል፤ ሁሉም ከመሸበር ወጥቶ የሚችለውን ያህል ቢታገል የአማራን ምድር እንዳይረግጡ ማድረግ እንደሚቻል ቀድመው አውቀዋል፡፡

ነፍጥ አንግበውም የሚችሉትን ያህል ታግለዋል፤ እዚያው ትግል ሜዳ ነው የምሞተው አልሸሽም ሲሉም በጓደኞቻቸው ግፊት ወደ ክምር ድንጋይ ተመልሰዋል፡፡

የጠላት ሃይል የሚችለውን ፕሮፓጋንዳ ነዝቶ ክምር ድንጋይን መቆጣጠሩ መላ ሰውነታቸውን ለህመም ዳርጎታል፡፡ ያም ሆኖ የሆቴሉን የንግድ ስራቸውን ባያቆሙም የ19 ዓመቱን ልጃቸውን ጌጥዬ ጌጤን ጨምረው ለትግል እራሳቸውን አዘጋጅተዋል፡፡

ሆቴላቸው አካባቢም ምሽግ ሠርተዋል፡፡ “እኔ ጌጤ እሬሳዬ ከቤት ይወጣል እንጂ ክምር ድንጋይን በፍርሃት ለቅቄ አልሄድም!” ብለውም ለራሳቸው ቃል ገብተዋል፡፡

የቤተሰባቸውን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ በተመለከተ ለወንድማቸው ለአቶ ሲሳይ ዳምጤ (የቀድሞው የአማራ ክልል ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ) ደውለው አደራ ሲሉ እንዲሸሹ አልመከራቸውም፡፡ ብትሠዋም ለሃገርህ ክብር ነውና የምትችለውን አድርግ፤ የምን መሸሽ ነው የሚል ምላሽ ይሰጧቸዋል፡፡

እኔም ፀረ ጁንታ ትግሉን እየመራሁ ጦር ሜዳ ነኝ፤ አንተ ከተሰዋህ ለቤተሰቦችህ እኔ አለሁ፡፡ እኔም ከተሰዋሁ ግን መንግስት ያሳድጋቸዋል፤ ታገል ይሏቸዋል፡፡

የቤተሰባቸውን ቀጣይ ማረፊያ በማደላደላቸው ደስ ብሏቸው ወደ ፀረ ጁንታ ትግል ዕቅዳቸው ይመለሳሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በውስጥ ባንዳዎች ጥቆማ አማካኝነት ሶስት ጁንታዎች ከተፍ ይላሉ፡፡ ልበ ሙሉ የክምር ድንጋዩ ጀግና ግን ለሶስት ጁንታዎች አልነካካም፤ መምጣታቸው ካልቀረማ ጠርቀም ይበሉ ብለው ከራሳቸው ጋር ይመክራሉ፡፡

በደቂቃዎች ልዩነት ተጨማሪ የጁንታው ታጋዮች ተግተለተሉ፤ አሁን ገድለው የሚሠውበት ጊዜ መቃረቡን አውቀዋል፡፡ 15ቱን ጁንታ ሬሳቸውን አጋድመው በጀግንነት ለመሰዋት ያሰቡትን እኒህን ጀግና ምግብ አቅርበው እንዲያበሏቸው የአሸባሪው ጁንታ ታጋዮች ይጠይቋቸዋል፡፡

ሳይቅማሙ መገቧቸው፤ ለነገር እንደፈለጓቸው ቀድሞ የገባቸው የክምር ድንጋዩ ነፍጠኛ መሳሪያቸውን አዘጋጀተዋል፡፡

ቀድመው ያዘጋጁትን መሳሪያ ይዘው የሚመጥናቸውን ቦታ ይዘዋል፡፡ ገድለው ለመሰዋት ቋምጠዋል፤ አላወላወሉም፡፡ ስድስቱን ጁንታዎች በአውቶማቲክ አርከፈከፉባቸው፡፡

ከውጭ የተቀመጡት አምስት ተጨማሪ የጠላት ኃይል አባላት በፍጥነት ወደ ቤት ገቡ፡፡ የእነ አይበገሬ ልጅ የሆኑት ጌጤ ግን ፍንክች አላሉም፡፡ ፍርሃት የለም፡፡

በሚለበልበው ክንዳቸው ሌላውን አውቶማቲክ በወኔ በጠላት ክንድ ላይ አሳርፈው እስከ ዘለዓለሙ ሸኟቸው፡፡

ይህም አልበቃ ሲላቸው የጠላትን የመገናኛ ሬዲዮና መሳሪያ ለማንሳት ሲታገሉ ከሆቴሉ ግቢ ውጭ የመጣው የጠላት ሃይል በቁጥር ጨምሮና ቦታ ይዞ ታገላቸው፤ አልተረቱም። የአባቶቻችን ገድል ፈፅመው ጫካ ገቡ።

የክምር ድንጋዩ አባ ረፍረፍ ጀብዱ ለብዙ ታጋዮች ትምህርት ሰጥቶ ለጠላት ረመጥ ሆኑ፡፡ ያሰቡትን የፈፀሙት አባ ረፍርፍ አስራ አንዱን አጋድመው ዕቅዳቸውን አሳኩ፡፡

አሁን ካለው ሁኔታ አኳያ መልዕክት እንዲያሥተላልፉ ሲጠየቁም “የልቤን በር የሚከፍት ቁልፍ ቢኖር ምንኛ ደስ ባለኝ ነበር?” ህዝባችን ለምን ይሸበራል? እኛ እኮ የጀግኖች ዘር ነን፤ የእነ አፄ ቴዎድሮስ፣ የአፄ ሚኒሊክ፣ የንጉስ ሚካኤል፣ የንጉስ ተክለ ሃይማኖት የአርበኛ በላይ ዘለቀ ልጆች ነን፡፡

ታሪክ የሠሩ አባቶቻችንን ብቻ እያስታወስን መኖሩ አይጠቅምም፡፡ የእራሳችንንም ታሪክ እንስራ፡፡ እንኳን በመሳሪያ አርበኛ በገጀራም ይዋጋል፡፡ አንድ ጥይት አንድ ጠላት ታስቀራለች፡፡ ታሪክ እንስራ ነው መልዕክቴ አሉን፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.