Fana: At a Speed of Life!

የዓለም ጤና ድርጅት ኮሮና ቫይረስ ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት መሆኑን አወጀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የዓለም ጤና ድርጅት መነሻውን ቻይና ያደረገውን የኮሮና ቫይረስ ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት ነው በሚል አወጀ።

ድርጅቱ ቫይረሱን በዓለም አቀፍ የጤና ስጋትነት ያወጀው ከቻይና ውጭ ወደ ሌሎች ሀገራት መዛመቱን ተከትሎ ነው ተብሏል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም እንዳስታወቁት፥ የኮሮና ቫይረስ በዓለም ጤና ስጋትነት የታወጀበት ዋነኛው ምክንያት በቻይና እየሆነ ባለው ሳይሆን በሌሎች የዓለም ሀገራት ላይ መሰራጨት በመጀመሩ ነው።

በተለይም የኮሮና ቫይረስ አሁን ባለበት ሁኔታ ደካማ የጤና ስርዓት ባላቸው ሀገራት ከተሰራጨ እጅግ አሳሳቢ መሆኑንም ነው ድርጅቱ የገለፀው።

ዶክተር ቴድሮስ አድሀኖም ቻይና በሽታውን ለመቆጣር እያደረገች ያለውን ሁሉን አቀፍ ጥረት በማድነቅ፥ ሀገራት ከቻይና ጋር የንግድ እና የጉዞ ግንኙነታቸውን የሚያቋርጡበት ምንም ምክንያት የለም ብለዋል።

ሆኖም ግን በርካታ ሀገራት ከቻይና ጋር ድንበራቸውን መዝጋታቸው እና የአውሮፕላን በረራ ያቋረጡ ሲሆን፥ እንደ ጎግል፣ ስታርባክስና ቴስላን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችም በቻይና ያላቸውን ቢሮ እየዘጉ ነው።

የአሜሪካ መንግስትም ዜጎቹ ወደ ቻይና ከመሄድ እንዲቆጠቡ የጉዞ ማስጠንቀቂያ ማውጣቱ ነው የተገለፀው።

በቻይና ብቻ እስካሁን በኮሮና ቫይረስ ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር 213 የደረሰ ሲሆን፥ በአጠቃላይ በሀገሪቱ ቁጥራቸው ወደ 10 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ከዚህ በተጨማሪም የኮሮና ቫይረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ በ18 ሀገራት የታየ ሲሆን፥ በእነዚህ ሃገራት 98 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል ይላል የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ።

ከእነዚህ ሃገራት ውስጥ በታይላንድ እና በጃፓን በ14 ሰዎች ላይ፣ በሲንጋፖር በ13 ሰዎች ላይ፣ በአውስትራሊያ እና ማሌዢያ በ8 ሰዎች ላይ፣ በደቡብ ኮሪያ 6 ሰዎች ላይ እንዲሁም በፈረንሳይ እና አሜሪካ በ5 ሰዎች ላይ ቫይረሱ መገኘቱም ነው የተገለፀው።

የዓለም ጤና ድርጅት የኖቭል ኮሮና ቫይረስ ከታሕሳስ 21 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በቻይና ውሃን ከተማ እንደተከሰተ ማስታወቁ ይታወሳል።

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.