Fana: At a Speed of Life!

ተመራማሪዎች ለኮሮና ቫይረስ ክትባት ለማግኘት ጥረት እያደረጉ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባለፉት አምስት ዓመታት ዓለም ላይ በተከሰቱት የኢቦላ እና ዚካ ቫይረሶች የበርካቶች ህይወት አልፏል ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችም ተከስተዋል።

ከሰሞኑም መነሻውን ቻይና ያደረገውና ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት እየተዛመተ የሚገኘው ኮሮና ቫይረስ ለምድራችን ስጋት ደቅኗል።

በቫይረሱ ምክንያት በሺህዎች የሚቆጠሩት ሰዎች ሲጠቁ ከ200 በላይ ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው አልፏል።

ተመራማሪዎችም አድማሱን እያሰፋ ላለው ቫይረስ ክትባት ለማግኘት ጥረት እያደረጉ ይገኛል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በአሜሪካ ሳንዲያጎ በሚገኝ ቤተ ሙከራ ተመራማሪዎች አዲስ የዲ ኤን ኤ ቴክኖሎጂን በመጠቀም፥ “አይ ኤን ኦ 4800” የተሰኘ ክትባት ለማሳደግ እየሰሩ ይገኛሉ።

ቤተ ሙከራው የቫይረሱን ክትባት ከመጭው ሰኔ ወር ጀምሮ ባለው ጊዜ የመሞከር እቅድ እንዳለውም አስታውቋል።

የመጀመሪያው ሙከራ ስኬታማ ከሆነም ከፍ ያሉ ተጨማሪ ሙከራዎች የቫይረሱ መነሻ በሆነችው ቻይና ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል።

ከዚህ ባለፈም በወረርሽኝ ስርጭት ፈጠራ እና በዓለም ዙሪያ ባሉ በጎ አድራጊ ማህበራት ትብብር ለኮሮና ቫይረስ ክትባት ለማግኘት በቤተ ሙከራ ምርምር እየተካሄደ ይገኛል።

በተቋሙ የክትባት ምርምር እና እድገት ዳይሬክተር ዶክተር ሜላኒ ሳቪል ተልዕኳችን “ወረርሽኙ ለሰው ስጋት አለመሆኑን ማረጋገጥ እና ክትባቱን ማግኘት ነው” ብለዋል።

ከአሜሪካው ምርምር ባለፈም በአውስትራሊያ ኩዊንስላንድ ዩኒቨርሲቲ እና ሞደሬኔና ኩባንያ እንዲሁም የዓለም ጤና ድርጅት ለቫይረሱ ክትባት ለማግኘት ምርምር እያረጉ ነው።

የቫይረሱ መነሻ በሆነችው ቻይና የቫይረሱ የዘረመል መለያ ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

ይህም የቫይረሱን መነሻ፣ የወረርሽኙኝ እድገትና መከላከያ መንገዱን ለማወቅ ይረዳል ነው የተባለው።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.