Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ የተሻሻለውን የኢንቨስትመንት አዋጅ አፀደቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሻሻለውን የኢንቨስትመንት አዋጅ አፀደቀ።

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በትናንትናው እለት ባካሄደው 12ኛ መደበኛ ስብሰባው በተሻሻለው የኢንቨስትመንት አዋጅ ላይ ተወያይቷል።

አዋጁ የግሉ ዘርፍ የነበረውን የኢንቨስትመንት ማነቆ እንደሚፈታና የውጭ ባለሀብቶች በዘርፉ በስፋት እንዲሰማሩ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

ለወጣቶች የስራ እድል የመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግና በኢንቨስትመንት ፖሊሲው ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ይፈታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተብራርቷል።

በአጠቃላይ በኢኮኖሚው ዘርፍ እየተካሄዱ ካሉ ለውጦች ጋር እንዲናበብና የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶች የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲጎለብት ለማስቻል የተዘጋጀ መሆኑም ተገልጿል።

የምክር ቤቱ አባላት በአዋጁ ላይ ሰፊ ውይይት ካደረጉበት በኋላ በ10 ተቃውሞና በአንድ ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቀውታል።

የተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 1180/2012 በሚል በመፅደቁ የቀድሞውን የኢንቨስትመንት አዋጅ ቁጥር 769/2005 ይተካል።

የቀድሞው የኢንቨስትመንት አዋጅ ለሰባት ዓመታት ስራ ላይ የዋለ መሆኑን የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.