Fana: At a Speed of Life!

ሁሉም የእርዳታ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሰሩ የሃገሪቱን ህጎችና መመሪያዎች ማክበር አለባቸው – ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 17 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁሉም የእርዳታ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሰሩ የሃገሪቱን ህጎችና መመሪያዎች ማክበር እንደሚገባቸው የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ ገለጹ።

ዶክተር ጌዲዮን ከቢቢሲ ሃርድ ቶክ ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቆይታ በኢትዮጵያ መንግስት ተወስዶ የነበረውን የህግ ማስከበር ዘመቻና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም አንዳንድ የእርዳታ ድርጅቶች በሃገሪቱ ያለውን ሁኔታ ለማባባስ ሙከራ ቢያደርጉም አብዛኞቹ መንግስት የወሰደውን የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ በበጎ በመውሰድ የሰብአዊ እርዳታ ስራቸው እያካሄዱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በመሆኑም ሁሉም የእርዳታ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሰሩ የሃገሪቱን ህጎችና መመሪያዎች ማክበር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ለግብርና ስራና ለእርዳታ ስርጭት ሲባል የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ ቢደረግም አሸባሪው ህወሓት ህጸናትና ሴቶችን ለጦርነት በማሰለፍ በአፋርና አማራ ክልሎች በፈጸመው ጥቃት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃንን በማፈናቀልና ብዙዎችን በመግደል የተኩስ አቁሙን ዋጋ እንዳሳጣው ጠቅሰዋል።

“በአፋር በኩል የተከፈተው የእርዳታ ማጓጓዣ መስመር በአሸባሪው ቡድን በመዘጋቱ ሰብአዊ እርዳታ በታሰበው ልክ ሊደርስ አልቻለም” ብለዋል።

አሸባሪው ቡድን የመልሶ ማልማት ስራዎች እንዳይተገበሩ የኤሌክትሪክና የቴሌኮም ባለሙያዎችን በመግደል አደጋ በመደቀኑ ጥገናውን ማድረግ እንዳልተቻለም ገልጸዋል።

“የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ነን የሚሉ ድርጅቶች የሚያወጧቸውን ሪፖርቶች ምርመራ የሚደረግባቸውና በቀላሉ የሚታለፉ አይደሉም” ያሉት ዶክተር ጌዲዮን፤ “አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያቀረባቸው ሪፖርቶች በጥንቃቄ በመመርመር እውነታዎችን አረጋግጠን ፍትህ ለማሰጠት ስራዎችን እየሰራን ነው” ብለዋል።

ምርመራዎች ባልተጠናቀቁበት ሁኔታ ድምዳሜ ላይ መድረስ የሽብርተኛውን ድርጅት ወንጀሎች ለመሸፈን የሚደረግ ጥረት እንደሚመስልም አመላክተዋል።

ህወሓት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ ስለተፈረጀ ለድርጅቱ የሚደረጉ ድጋፎች ሁሉ ወንጀሎች ናቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አሸባሪው ህወሓት ለሶስት አስርት አመታት የዘለቀ አምባገነናዊ አገዛዝ ቢያሰፍንም የህዝቡን ስነልቦና ማሸነፍ እንዳልቻለም ገልጸዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.