Fana: At a Speed of Life!

በቦሌ ክፍለ ከተማ 20 ክላሽንኮቭ ጠመንጃዎች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 18፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)በቦሌ ክፍለ ከተማ በሚገኝ አንድ ፔንሲዮን የተደበቁ 20 ክላሽን-ኮቭ ጠመንጃዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለፀ፡፡

በወንጀሉ የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች ተይዘው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝም ፖሊስ አስታውቋል፡፡

ትናንት ምሽት በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት ልዩ ቦታው ውሃ ልማት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው አምባሳደር ፔንሲዮን ውስጥ የመኝታ አገልግሎት ፈልገው አልጋ ለመከራየት የገቡ ሁለት ግለሰቦች በማዳበሪያ የተጠቀለለ ለጊዜው ምንነቱ ያልታወቀ ነገር ይዘው ስለመግባታቸው በክትትል ተደርሶባቸዋል፡፡

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጥብቅ ጥናትና ክትትል ሲያደርግ ከቆየ በኋላ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመቀናጀትና አስፈላጊውን ህጋዊ ሂደት በመከተል በፔንሲዮኑ ውስጥ ባደረገው ብርበራ በጨርቅ እና በማዳበሪያ የተጠቀለሉ አስር ባለሰደፍ እና አስር ታጣፊ ክላሽን-ኮቭ ጠብመንጃዎችን እንዲሁም 17 የክላሽንኮቭ ጥይት ካርታዎችን በመኝታ ክፍል ውስጥ ተደብቀው መገኘታቸውንና በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ ገልጿል፡፡

ከውስጥ እና ከውጪ ፀረ- ሰላም ሃይሎች ጋር ተጣምረው ሃገራችንን ለማፍረስ እየሰሩ የሚገኙት የሽብር ቡድኖች ተልዕኳቸውን ለማሳካት የተለያዩ መንገዶችን ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ተጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ ለማድረግ አልጋ የሚያከራዩ ሆቴሎች፣ ፔንሲዮኖች እና መሰል አገልግሎት የሚሰጡ የንግድ ተቋማት እንዲሁም የመኖሪያ ቤት የሚያከራዩ ግለሰቦች የተከራዮችን ማንነት በደንብ ማረጋገጥ እና አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙ ለፀጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበር የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳስቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.