የኮሮና ቫይረስን ለመከላከልና የለይቶ ማከሚያ የህክምና ማዕከላት የቅድመ ዝግጅት ስራ ተጎበኘ
አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኖቭል ኮሮና ቫይረስ አስቀድሞ መከላከል እና የለይቶ ማከሚያ የህክምና ማዕከላት ላይ እየተሰራ ያለው የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ላይ ጉብኝት ተካሄደ።
የጤና ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካዮች እና የሲዲሲ ተወካዮች የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ተዘዋውረው መጎብኘታቸውን የጤና ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ ያመለክታል።
መነሻውን ቻይና ያደረገው የኖቭል ኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ የቅድመ መከላከልና ጥንቃቄ እንዲሁም የድንገተኛ አደጋ ምላሽ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል።
ከዚህ ውስጥም በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሚደረግ የሰውነት የሙቀት ልየታ ስራ እና ጊዜያዊ የለይቶ መከታተያ ክፍል ይገኙበታል።
የጤና ሚኒስትር ዲኤታ፣ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካዮች እና የሲዲሲ ተወካዮች በየተቋማቱ ጉብኝት ካደረጉ በኋላ አጠቃላይ የቅድመ ዝግጅትና ፈጣን ምላሽ ስራዎች ላይ ምክረ ሃሳቦችን ሰጥተዋል።