Fana: At a Speed of Life!

በብሪታንያ ሁለት የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ተገኙ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 22 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በብሪታንያ ሁለት የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች መገኘታቸው ተነገረ።

ግለሰቦቹ የአንድ ቤተሰብ አባላት ሲሆኑ፥ ኒውካስትል በሚገኝ ልዩ የህክምና ማዕከል ክትትል እየተደረገላቸው ነው ተብሏል።

83 የብሪታንያ ዜጎች እና 27 የተለያዩ ሃገራት ዜጎች የቫይረሱ መነሻ ከሆነችው ውሃን ከተማ ወደ ብሪታንያ መግባታውም ታውቋል።

የቫይረሱ ተጠቂዎች ተገኙ ከመባሉ ባለፈ ግን የወጣ ዝርዝር መረጃ የለም።

ከዚህ ባለፈም ሩሲያም ሁለት የቫይረሱን ተጠቂዎች ማግኘቷን አስታውቃለች።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ታቲያና ጎሊኮቫን ዋቢ ያደረገው የአር ቲ ዘገባ ሩሲያን ከሩቅ ምስራቅ በሚያዋስነው ክልል የቫይረሱ ተጠቂ የሆኑ ሁለት ቻይናውያን ዜጎች መገኘታቸውን ያመላክታል።

የቫይረሱ ተጠቂዎች አሁን ላይ ለብቻቸው በልዩ የህክምና ክትትል ውስጥ እንደሚገኙም ዘገባው ያስረዳል።

ከውሃን ከተማ በተነሳው ኮሮና ቫይረስ ሳቢያ እስካሁን 213 ሰዎች ለህልፈት ሲዳረጉ ወደ 10 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ መያዛቸው ተነግሯል።

ከቻይና ውጭ ባሉ ሃገራት ደግሞ 98 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል ነው የተባለው።

ቫይረሱ እስካሁን በንክኪ ከሰው ወደ ሰው የተላለፈ ሲሆን፥ በዚህ ሂደት 8 ሰዎች ተጠቂ መሆናቸውም ተነግሯል።

ደቡብ ኮሪያም በዛሬው እለት አራት ተጨማሪ የቫይረሱ ተጠቂዎች መኖራቸውን ገልጻለች።

የቫይረሱን ስርጭት ተከትሎም በርካታ ሃገራት የቻይና በረራዎችን ሰርዘዋል፤ ጀርመን እና ቱርክ ደግሞ በቻይና የሚገኙ ዜጎቻቸውን በወታደራዊ አውሮፕላን ለማምጣት ዝግጅት ጀምረዋል።

ሞንጎሊያ ደግሞ ከቻይና ጋር የሚያዋስናትን ድንበር እስከ የካቲት ወር መጨረሻ ድረስ እንደምትዘጋ አስታውቃለች።

የጤና ባለሙያዎች የቫይረሱ ስርጭት አደገኛ የሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ሲገልጹ የዓለም ጤና ድርጅት ደግሞ ቫይረሱ ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት መሆኑን አውጇል።

ተመራማሪዎች ደግሞ ለቫይረሱ ክትባት ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ እና አልጀዚራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.