Fana: At a Speed of Life!

በሽፍቶቹ ላይ ተወሰደው እርምጃ በህዳሴ ግድብ አካባቢ ጥቃት መሰንዘር እንደማይቻል  ለውጭና ለውስጥ ጠላቶች ትምህርት የሰጠ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በህዳሴ ግድብ  አካባቢ ሰርገው ለመግባትና ሽብር ለመፍጠር ያሰቡ ቡድኖች ላይ የተወሰደው ወታደራዊ እርምጃ የማያዳግምና ለቀጣይ ትምህርት የሰጠ እንደነበር ተገለፀ።

መንግስት ያቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ ያልተቀበሉ የጉምዝ ታጣቂዎችን ሽብርተኛው በሱዳን አሰልጥኖና አስታጥቆ በአልመሃል አቅጣጫ ጥቃት ለማድረስና የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ለማደናቀፍ ሙከራ አድርጎ እንደነበር ፤ የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ሀይል ኮማንድ ፖስት ዋና ሰብሳቢ ሌተና ጄኔራል አስራት ዴኔሮ አስታውሰዋል።

ጄኔራሉ  ከመከላከያ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ፥የመከላከያ ሰራዊትና በቀጠናው የተሰማሩ የክልል ልዩ ሀይሎች ለተከታታይ ሶስት ቀናት በአሸባሪው ተላላኪዎች ላይ በወሰዱት እርምጃ ሀገር እና ህዝብን የሚያኮራ ጀብዱ መፈፀማቸውን ተናግረዋል።

በሽፍቶቹ ላይ በተወሰደው የማያዳግም እርምጃ የሰራዊታችን ጀግንነትና ፅናት ጎልቶ የታየበት አጋጣሚ መሆኑን ያነሱት ዋና ሰብሳቢው ፥ በህዳሴ ግድብ አካባቢ ጥቃት መሰንዘር እንደማይቻል ለሌሎች የውጭና የውስጥ ጠላቶችም ትምህርት ሰጥቶ ማለፉን ነው ያረጋገጡት።

የሰራዊታችንን ምት መቋቋም ያልቻለው ይህ የህወሀት አሽከር ሽፍታ ባረፈበት ከባድ ምት ተበታትኖ ወደ ሱዳን ደማዚን የሸሸ ሲሆን ፤ የአካባቢው ስጋት መሆን ወደ ማይችልበት ደረጃ ለማድረስ እግር በእግር እየተከታተሉ የመደምሰስ ስራው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ጄኔራሉ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ስራ ለደቂቃ ሳይቋረጥ በመካሄድ ላይ መሆኑን የገለፁት ጄኔራል አስራት የፀጥታውን አስተማማኝነት ለማረጋገጥ ሰራዊታችን ማንኛውንም መሰዋእትነት እየከፈለ እንደሚገኝና ይህን ለማድረግ አስተማማኝ ዝግጁነት እንዳለው  ከመከላያ ሰራዊት የፌስ ቡክ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ባሳለፍነው ሳምንት በቀጠናው ሰራዊቱ  ባደረገው ውጊያ ከ170 በላይ የጥፋት ሀይሎች መደምሰሳቸው ይታወሳል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.