80ኛው የሰባት ቤት አገው ፈረሰኞች ማኅበር በዓል ዛሬ ተከረ
አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 80ኛው የሰባት ቤት አገው ፈረሰኞች ማኅበር በዓል በዛሬው እለት በእንጅባራ ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም፣ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ላቀ አያሌው እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለበዓሉ ታዳሚያን እንኳን አደረሳችሁ ብለው ከእለት እለት ኑሮ እስከ አርበኝነት ድል ለዘለቀው የፈረሰኞች ታሪካዊነት በተለይም ለአዊ ህዝብ ያለውን ትርጉም አውስተዋል።
ሃገራቱ በጣም በሚያጎመጁ ተስፋዎች እና በሚፈታተኑ ተግዳሮቶች ውስጥ እንደምትገኝ የጠቆሙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ፤ ጉዟችን አንድ እርምጃ ወደፊት አንድ እርምጃ ወደ ኋላ ሊሆን አይገባም ብለዋል።
ትውልዱ ሃገሪቱ ከገጠመት ፈተና በዘላቂነት የሚያሻግረውን መንገድ በጥንቃቄ እና በማስተዋል መከተል እንዳለበት አሳስበዋል።
በየዓመቱ ኢትዮጵያውያን የቀደሙ አባቶቻቸው ተጋድሎ ለመረዳት፤ የአዊን ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
በአዊ ብሄረሰብ ትልቅ ስፍራ ያለው የሰባት ቤት አገው ፈረሰኞች ማኅበር በዓል ዋነኛው ዝግጅት የሆነው የፈረሰኞች ጉግስ ትዕይንት ከ2ሺ በላይ ፈረሰኞች በተገኙበትም ተካሂዷል።
የሰባት ቤት አገው ፈረሰኞች ማኅበር በዓል ከ1932 ዓ.ም አንስቶ አንዴም ሳይቋረጥ ነበር መከበር የጀመረ ሲሆን፥ በወቅቱ በጥቂት አባላት የጀመረው ማህበሩ አሁን ላይ ከ52 ሺህ በላይ አባላት አሉት።
በፈረስ ጉግስ ትርዒቱ ላይ በርካታ ሴቶች ጨምሮ ዐይነስውር ፈረሰኛ መሳተፉም አስደናቂ የትርዒቱ አካል ነበር።
በአክሱማዊት ገብረህይወት