Fana: At a Speed of Life!

የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማ መገርሳ ከፈረንሳይ አቻቸው ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር አቶ ለማ መገርሳ ከፈረንሳይ የመከላከያ ሚኒስትር ፍሎረንስ ፓርሊ ጋር ተወያዩ።

በመከላከያ ሚኒስትሩ የሚመራውና ከፍተኛ መኮንኖችን የያዘው የኢትዮጵያ ልዑክ በፈረንሳይ ፓሪስ ጉብኝት እያደረገ ይገኛል።

በዛሬው እለትም የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ለማ መገርሳ በፓሪስ ደ ብሪየን ፓላስ ከፈረንሳይ የመከላከያ ሚኒስትር ፍሎረንስ ፓርሊ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም የኢትዮጵያን የባህር ኃይል ወደ ስራ ለማስገባት እና የአየር ኃይል ለማዘመን ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ተስማምተዋል።

ከስብሰባው አስቀድሞ አቶ ለማ የክብር ዘብ አቀባበል እንደተደረገላቸው በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ አስታውቀዋል።

በመቀጠልም በፓሪስ ኤሊዜ ቤተ መንግስት ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ከፕሬዚዳንቱ ኤታ ማዦር ከአዲሚራል በርናርድ ሮዤል ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።

የኢትዮጵያ ልኡክ ከዚህ ቀደም ከፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ተወያዩ ዢያን ባብቲስት ሌሞይን ጋር ተገናኝቶ በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ይታወሳል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.