Fana: At a Speed of Life!

ኤሌክትሪክ አገልግሎት 58 ሚሊየን ዶላር የፈጀ ዘመናዊ የመረጃ ቴክኖሎጂ መተግበሪያ አስመረቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ58 ሚሊየን ዶላር ወጪ ዘመናዊ የመረጃ ቴክኖሎጂ መተግበሪያ ፕሮጀክት አስመረቀ።

ኢ.አር.ፒ /ኢንተርፕራይዝ ሪሶስር ፕላኒንግ/ የተሰኘው ይህ መተግበሪያ የተቋሙን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ከማሳደግ ባሻገር ለተገልጋዮች ቀልጣፋ፣ ግልፅና ተጠያቂነት ያለው አገልግሎት መስጠት ያስችላል ተብሏል።

ከመተግበሪያው በተጨማሪ ድርጅቱ የተጓዳኝ ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ፕሮጀክትም አስመርቋል።

የተቋሙ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ እና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።

የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ፥ ፕሮጀክቱ ፍትሀዊ፣ ፈጣን፣ ቀልጣፋና ግልፅ አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር የኃይል ብክነትን ለመቀነስና የተቋሙንም ገቢ ለማሳደግ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

ድርጅቱ ራሱን ለማዘመን በርካታ ቴክኖሎጂዎችን ለመተግበር እየሰራ ሲሆን፥ በዘርፉ ልምድ ካለው ከህንዱ ቴክ ማሂንድራ ኩባንያ ጋር በ2008 ዓ.ም የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት ላለፉት አራት ዓመታት ሲተገበር መቆየቱና ውጤታማነቱ መረጋገጡ ተወስቷል።

መተግበሪያው ለዕለታዊ ተግባር የሚያስፈልግ ሀብትና ግብዓትን ማቀናጀት፣ የመረጃ ፍሰትን ማሳለጥ፣ መረጃዎችን በአንድ ቋት ፈጥሮ ወጥነት ባለው መልኩ ማቀናጀት የሚያስችል ነው።

ለማምረቻ፣ ለግዥና አቅርቦት ስርጭት፣ ለሂሳብ አያያዝ፣ ለግብይት፣ ለደንበኞች መስተንግዶ፣ ለሰው ኃይል ቁጥጥርና ሌሎችም ዘርፎችም አገልግሎት ይሰጣል።

ለተጠቃሚዎች የተቀናጀ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠትና የተጠቃለለና የተደራጀ ሪፖርት ለማግኘት እንደሚያግዝም ተጠቁሟል።

የቦርድ ሰብሳቢው ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ የስራ አመራር ቦርዱ መንግስት ለኃይሉ ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ ቢሰራም ለተጠቃሚዎች የሃይል ውስንነት መኖሩ የቅሬታና መልካም አስተዳደር ምንጭ እንደሆነ ገልጸዋል።

በቴክኖሎጂ ያልተደገፈና አሰራሩም ኋላቀር በመሆኑ ደንበኞችን ያላረካ መሆኑንም ገልፀዋል።

ተቋሙ ራሱን አዘምኖ ውጤታማ እንዲሆን መፍትሄዎችን ማስቀመጡን ጠቅሰው አሰራሩን ያልተማከለ ማድረግ፣ የጥገናና መሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን ለሶስተኛ ወገን መስጠትና የውስጥ አሰራሩን በቴክኖሎጂ መቀየር ናቸው ሲሉ አብራርተዋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.