Fana: At a Speed of Life!

የአረብ ሊግ በፕሬዚዳንት ትራምፕ የመካከለኛው ምስራቅ እቅድ ላይ አስቸኳይ ስብሰባ ተቀመጠ

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአረብ ሊግ ሀገራት በአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመካከለኛው ምስራቅ እቅድ ዙሪያ አስቸኳር ጉባዔ እያደረጉ ይገኛሉ።

በግብፅ ካይሮ እየተካሄደ ያለው አስቸኳይ ስብሰባው በፊሊስጤም አስተዳደር ፕሬዚዳንት መሃሙድ አባስ ጥያቄ አቅራቢነት የተጠራ መሆኑም ነው የተነገረው።

ፕሬዚዳንት መሃሙድ አባስ የአረብ ሊግ አባል ሀገራት ፕሬዚዳንት ትራምፕ “የክፍለ ዘመኑ ስምምነት” ባሉት እቅዳቸው ላይ ያላቸውን ግልፅ ተቃውሞ እንዲያቀርቡ በማሰብ አስቸኳይ ስብሰባው እንዲጠራ መጠየቃቸውም ተሰምቷል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አዲሱን የመካከለኛው ምስራቅ የሰላም እቅድ ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን፥ እቅዱ ከፍልስጤማውያን በኩል ምንም አይነት ግብአት እንዳልተካተተበት ተነግሯል።

የአረብ ሊግ አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እየተሳተፉበት ባለው ስብሰባ ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት መሃሙድ አባስ፥ “ፕሬዚዳንት ትራምፕ እቅዱን እንዳነብ እንደሚፈልግ ነግረውኝ ነበር፤ እኔ ግን አላነብም አልኩ” ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ፕሬዚዳንት ትራምፕ በስልክ ሊያናግሯቸውም ፈልገው እምቢ እንዳሉ እና ከፕሬዚዳንቱ የተላከ ደብዳቤንም አልቀበልም ማለታቸውን አስታውቀዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር በመሆን አዲሱን የመካከለኛው ምስራቅ የሰላም እቅድ ባሳለፍነው ማክሰኞ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የፕሬዚዳንቱ እቅድ የእስራኤል እና ፍልስጤም የግጭት መንስኤ የሆነችው እየሩሳሌም ከተማን የእስራኤል አይነኬ ከተማ አድርጎ የሚያስቀጥል ሲሆን፥ ዌስት ባንክ የእስራኤል ሉዓላዊ ግዛት መሆኗን በእቅዳቸው ይፋ አድርገዋል።

ፍልስጤማውያን በበኩላቸው የትራምፕን እቅድ ተቃውመው በራማላህ ቁጣቸውን የገለፁ ሲሆን፥ “ፍልስጤምን ያለ ምስራቅ እየሩሳሌም ማሰብ አይቻልምም” ሲሉም ተሰምተዋል።

ምንጭ፦ www.aljazeera.com

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.