Fana: At a Speed of Life!

ፍልስጤም ከአሜሪካ እና እስራኤል ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት አቋረጠች

አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ፍልስጤም ከአሜሪካ እና እስራኤል ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግነኙነት ማቋረጧን አስታውቃለች።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለዘመናት የቆየውን የእስራኤል እና ፍልስጤም ግጭት ብሎም የቀጠናውን ሰላም በዘላቂነት መፍታት ያስችላል ያሉትን የሰላም እቅድ በቅርቡ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ይህን ተከትሎም የዓረብ ሊግ ሀገራት በትናንትናው ዕለት በጉዳዩ ዙሪያ የሚመክር አስቸኳይ ጉባኤ በግብጽ ካይሮ አካሂደዋል።

ሀገራቱ  ባካሄዱት ስብሰባም ትራምፕ ይፋ ያደረጉት የሰላም እቅድ የፍልስጤማውያንን መብት በዘላቂነት የማያስከብር በማለት ውድቅ አድርገውታል።

የፍልስጤም ፕሬዚዳንት  መሃሙድ አባስ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ሀገራቸው ከአሜሪካ እና እስራኤል ጋር የነበራትን ሁለንተናዊ ግንኙነት ማቋረጧን አስታውቀዋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ይፋ ያደረጉትን የሰላም እቅድ የፍልስጤማውያንን ጥቅም እና መብት  የማያስከበር ከመሆኑ ባሻገር ዓለማቀፋዊ ህግን ያልተከተለ የፖለቲካ ሴራ ሲሉ አጣጥለውታል።

የፕሬዚዳንት ትራምፕ  የመካከለኛው ምስራቅ የሰላም እቅድ የእስራኤልና ፍልስጤም የዘመናት ግጭት መንስኤ የሆነችው እየሩሳሌም ከተማን የእስራኤል ግዛት ስለመሆኗ እውቅና ይሰጣል።

ዌስት ባንክ የእስራኤል ሉዓላዊ ግዛት መሆኗን የሚያረጋግጠው የሰላም እቅዱ፥ ፍልስጤማውያንም ሆኑ እስራኤላውያን አሁን ላይ ከሚኖሩበት ስፍራ የማይለቁ መሆኑንም ያብራራል።

በሌላ በኩል የሰላም እቅዱ ለፍልስጤም ሉዓላዊ ሀገር ምስረታ እውቅና የሚሰጥ መሆኑ ተመላክቷል።

ምንጭ፦presstv.com

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.