Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በዱባይ ሊወያዩ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በዱባይ ሊወያዩ ነው።

በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ፥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከየካቲት 5  እስከ የካቲት 7 ቀን 2012 ዓመተ ምህረት ድረስ ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ከተውጣጡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር የሚወያዩበት መድረክ ተዘጋጅቷል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ ግንዛቤ የሚያገኙበት ብቻ ሳይሆን ዜጎች በየሚኖሩባቸው ሀገራት መብትና ክብራቸው ተጠብቆ እየኖሩ በሀገራቸው ውስጥ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የለውጥ ሂደትም ተሳታፊ ሊሆኑ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ውይይት እንደሚያደርጉ ኤምባሲው አስታውቋል።

በዚህ መድረክ ላይ ከሳዑዲ አረቢያ፣ ሊባኖስ፣ ኩዌት፣ ኦማን፣ ካታር እና ባህሬን የተውጣጡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ይሳተፋሉም ብሏል።

ህዝባዊ መድረኩ ስኬታማ እንዲሆን በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚገኙ የአቡዳቢ ኤምባሲ እና የዱባይ ቆንስላ ፅህፈት ቤት የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመፍጠር ሰፊ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑ ተመልክቷል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተደራጅተው የዝግጅቱ አካል በመሆን እየሰሩ እንደሚገኙ ኤምባሲው ግልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.