የዳውሮ ዘመን መለወጫ በኮይሻ ጋቲ ጋጿ ተከበረ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የዳውሮ ዘመን መለወጫ ‘ቶኪ በዓ’ በዓል በዞኑ የነገስታት መናገሻ በሆነው ኮይሻ ጋቲ ጋጿ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
ቅርሶችን በማልማት ለኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማዋል የተጀመሩ ጥረቶችን ማስቀጠል ተገቢ መሆኑን የዳዉሮ ዞን አስተዳደር አስታውቋል፡፡
የብሄሩ መገለጫ የሆነው የቶኪ በዓ በዓል ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር መቆየቱ ይታወቃል።
ይሁን እንጂ የዘንድሮው የዘመን መለወጫ በዓል የሃገር ክብርን ለማስጠበቅ እየተዋደቁ የሚገኙ የሃገር መከላከያ ሠራዊትን በማሰብ እንዲሆንና በዞኑ ከእይታ ውጪ የሆኑ ከ450 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ የ16 ነገስታት መናገሻን መልሶ ለማልማት ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በሥፍራው የተገኙ የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተክሌ በዛብህ እንደገለጹት÷ የብሄሩ የማንነቱ መገለጫ የሆነው ባህል፣ ቅርስና ታሪክ ይበልጥ ህዝባዊ መሠረት እንዲኖረው በማድረግ ከዘርፉ የሚጠበቀውን ኢኮኖሚ ለማስገኘት አስተዳደሩ በትኩረት እየሠራ ይገኛል።
በጉብኝቱ ከ10 ወረዳዎችና ሁለት የከተማ አስተዳደር መዋቅሮች እና ከዞኑ የተለያዩ መምሪያዎች የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
በዕለቱ በነገስታቱ መናገሻ የሚገኙ የድንጋይ ላይ ገበጣ፣ የድንጋይ ሙቀጫ፣ የድንጋይ እንስራ፣ የድንጋይ ላይ እሳት ማንደጃ፣ የነገስታቱ ዙፋንና መናፈሻዎች መጎብኘታቸውን ደሬቴድ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!