Fana: At a Speed of Life!

ቻይና አሜሪካ የኮሮና ቫይረስን አስመልክቶ ስጋት እያሳደረች ነው ስትል ወቀሰች

አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ቻይና አሜሪካ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን አስመልክቶ በሰዎች ዘንድ ስጋትን እያሳደረች ነው ስትል ወቀሰች።

ባለፈው ሳምንት አሜሪካ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ብሄራዊ የጤና ስጋት ነው በማለት ማወጇ እና ለሁለት ሳምንታት ቻይናን የጎበኙ የውጭ ሀገራት ዜጎችም ወደ ሀገሯ እንዳይገቡ መከልከሏ ይታወሳል።

ይህን አዋጅ ተከትሎም ቻይና አሜሪካ ቫይረሱን ለመከላከል ድጋፍ ከመስጠት ይልቅ ሰዎች ዘንድ ስጋትን በማባባስ ላይ ትገኛለች ትስል ወቅሳለች።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ሁዋ ቹንግኒ በሰጡት መግለጫ፥ አሜሪካ እርዳታ ከመስጠት ይልቅ ዜጎቿን በማስወጣት እና ጉዞን በመገደብ ፍርሃትን በማስፋፋት ላይ ትገኛለች ብለዋል።

እንደ አሜሪካ ያሉ በሽታን የመቆጣጠርና የመከላከል አቅማቸው ከፍተኛ የሆኑ የበለጸጉ ሀገራት ከዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት ምክሮች ጋር የሚጋጭ ውሳኔ እያሳለፉ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ቃለ አቀባይዋ አያይዘውም ሀገራት ምክንያታዊ፣ የሚያረጋጋ እና በሳይንስ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ መስጠት አለባቸው ነው ያሉት።

በቻይና እና አሜሪካ መካከል የነበረው ግንኙነት በንግድ ጦርነት ለረጅም ጊዜ ከሻከረ በኋላ ማገገም ጀምሮ ነበር።

በቻይና ውሃን ግዛት በተቀሰቀሰው እና አሁን ላይ ሁሉንም የቻይና ግዛቶች ባደረሰው የኮሮና ቫይረስ እስካሁን ከ17 ሺህ በላይ ሰዎች የተያዙ ሲሆን 361 ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋል።

ቫይረሱ ከቻይና ውጭ በ23 ሀገራት በመሰራጨት ከ150 ሰዎች ላይ የታየ ሲሆን፥ ከቻይና ውጭም በኮሮና ቫይረስ የመጀመሪያው ሞት በፊሊፒንስ ተከስቷል።

ምንጭ፡-ሬውተርስ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.