Fana: At a Speed of Life!

በአጣዬና አካባቢው በነበረው ግጭት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች መልሶ የማቋቋም ስራ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 2፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በአጣዬ እና አካባቢው በነበረው ግጭት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች መልሶ የማቋቋም ስራ እየተሰራ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር አህመዲን መሃመድ ገለፁ፡፡

በዛሬው እለት በአጣዬ ከተማ ቤት ንብረታቸው ለወደመባቸው ነዋሪዎች በተለያዩ አካላት የተገነቡ ጊዜያዊ መጠለያ ቤቶችን ዶክተር አህመዲን መሃመድ፣ የአጣዬና አካባቢው ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ሌተናል ጀነራል ደስታ አብቼ፣ የአማራ ክልል ንግድና ኢንደስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ፣ የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረፃዲቅ፣ የአጣዬ ከተማ ከንቲባ አቶ አገኘሁ መክቴ አስረክበዋል።

በጊዜያዊነት ከተገነቡት 64 መጠለያዎች በተጨማሪ በቋሚነት በከተማዋ ለሚገነቡ ቤቶች ደግሞ ግንባታ ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት መካሄዱን ሚኒስትር ዲኤታው በፌስቡክ ገፃቸው አስፍረዋል፡፡

ከኤፍራታና ግድም ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሰለሞን አልታዬ ጋር በመሆንም በቆሪ ሜዳ እየተገነቡ ያሉ ቤቶች ተጎብኝተዋል።
አካባቢው ብዝሃነትን የሚያስተናግድ በመሆኑ ይህንን ብዝሃነት ጠላቶቻችን ለግጭት ሊጠቀሙበት ፍላጎት ስላላቸው ይህንን በመገንዘብ ሁላችንም ለሰላማችን ዘብ መቆም ይኖርብናል ሲሉም ዶክተር አህመዲን አሳስበዋል፡፡

ሀገር አጥፊ የሆነው የመከፋፈልና የግጭት አካሄዶች ከህወሃት የሽብር ቡድን ጋር አብሮ እንደሚቀበር እርግጠኞች ነን ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው የአጣዬ ከተማ ከደረሰባት ጉዳት እንድታገግም እየሰሩ ላሉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.