በመንገድ ደህንነት ግምገማ ጥናት ዙሪያ ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የትራንስፖርት ሚኒስቴር ኢፒቲሳ ከተባለ ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት ጋር በሚያከናውነው የመንገድ ደህንነት ግምገማ ጥናት ዙሪያ ውይይት አካሄደ።
ደህንነታቸውን ባልጠበቁ መንገዶች ምክንያት የሚከሰተውን የትራፊክ አደጋ ለመከላለከል በሀገሪቱ የተመረጡ መንገዶች ላይ የመንገድ ደህንነት ግምገማ በማካሄድ የማሻሻያ ስራዎችን ለመስራት ታስቧል።
በዚህ መሰረት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ኢፒቲሳ ከተባለ ዓለም አቀፍ የስፔን አማካሪ ድርጅት ጋር የመንገድ ደህንነት ግምገማ ጥናት እያከናወነ ነው።
ድርጅቱ አደጋ በብዛት በሚከሰትባቸው በተመረጡ 10 የመንገድ ኮሪደሮች ከአዳማ አዋሽ፣ ከሚሌ ጋላፊ፣ ከመቐለ አዲግራት፣ ከአዲስ አበባ ኮምቦልቻ፣ ከአዲስ አበባ ደብረማርቆስ፣ ከአዲስ አበባ ነቀምት፣ ከአዲስ አበባ ጅማ፣ ከሻሸመኔ ሶዶ፣ ከሻሸመኔ ዲላ እንዲሁም የአዲስ አዳማ የክፍያ መንገዶች ጨምሮ የ2 ሺህ ኪሎ ሜትር የግምገማ ጥናቶቹን በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል።
ድርጅቱ በተመረጡት ኮሪደሮች ላይ በሁለቱም የመንገድ አካፋዮች የተንቀሳቃሽ ምስል (ቪዲዮ) መረጃ በመውሰድ የመንገድ ፍተሻ አድርጓል።
በመሆኑም መንገዱ በሚያቋርጥባቸው 79 ወረዳዎች ላይ በአጠቃላይ 8 ሺህ 166 በትራፊክ ፖሊስ ጽህፈት ቤት በየዕለት የተመዘገቡ የትራፊክ አደጋ መረጃዎችን በመልቀም እና በኮሪደሮቹ ላይ ያለውን የዓመት አማካይ የትራፊክ መጠንን በመውሰድ የትንተና ሪፖርት ለትራንስፖርት ሚኒስቴር የብሔራዊ መንገድ ደህንነት ጽህፈት ቤት ማቅረቡም ታውቋል።
በትንተናው መሰረት ከ2 ሺህ ኪሎ ሜትሩ መንገድ ውስጥ የመንገድ ደህንነት ኦዲት የሚሰራባቸውን ሶስት የኮሪደር መስፈርቶች፣ በቀጣይ ስልጠና ለመስጠት በተዘጋጀው የመነሻ ምክረ ሃሳብ ውይይት መደረጉን ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።