የሀገር ውስጥ ዜና

ከመቅደላ ተዘርፈው የተወሰዱ የኢትዮጵያ ቅርሶች ተመለሱ

By Meseret Awoke

September 09, 2021

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)ከመቅደላ ተዘርፈው የተወሰዱ የኢትዮጵያ ቅርሶች በለንደን ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተመልሰዋል፡፡

በ1868 በአጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግስት በመቅደላ ጦርነት የተዘረፉ የኢትዮጵያ ቅርሶች በይፋ ለኤምባሲው ተመልሰዋል።

ከተመለሱ ቅርሶች መካከል በእጅ የተጻፈ መጽሐፍ ቅዱስ፣ መስቀሎች፣ በዘመኑ ለጦርነት ይጠቀሙባቸው የነበረ የጦር ጋሻ፣ ከቀንድና በብር የተለበጡ ዋንጫዎች እና ማንኪያዎች እና የጳጳስ አክሊል እና ሌሎች ቅርሶች ይገኙበታል፡፡

የቅርሶቹን ርክክብ መርሃ ግብር የአቴናየም ክለብ ያሰናዳው ሲሆን÷ በመርሃ ግብሩ አምባሳደር ተፈሪ መለሰን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ተገኝተዋል፡፡

በዚህ ወቅት ንግግር ያደረጉት አምባሳደር ተፈሪ መለሰ ሼሄራዜድ የእንግሊዝ የበጎ አድራጎት ድርጅት ከለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በቅርሶቹ ዙሪያ ለወራት ድርድር እንዲደረግ እና ለሽያጭ ቀርበው የነበሩትን ከገበያ እንዲነሱ በማድረግ ቅርሶቹ ለባለቤቱ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲመለሱ በመወሰኑ አመስግነዋል።

የሼሄራዜድ በጎ አድራጎት መስራች ጣሂር ሻህ በበኩላቸው÷ የቅርሶቹ መመለስ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ማለት እንደሆነ እንደሚያውቁና የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር እንደሚሆን መግለጻቸውን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!