የሀገር ውስጥ ዜና

በቀዳማዊ እመቤት ፅ/ቤት በ800 ሚሊየን ብር የዳቦና ዱቄት ፋብሪካዎች ሊገነቡ ነው

By Alemayehu Geremew

September 09, 2021

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት እና ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በአስር ከተሞች ለሚሰሩ አስር የዳቦ እና የዱቄት ፋብሪካዎች ግንባታ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ፡፡

ዳቦ ቤቶቹ በአስር ከተሞች የሚገነቡ ሲሆን÷ የዳቦና የዱቄት ፋብሪካዎችን በአንድ ላይ አጣምረው የሚይዙ ይሆናል ነው የተባለው፡፡

የሚገነቡት ፋብሪካዎች እያንዳንዳቸው በቀን 400 ኩንታል ዱቄት የማምረት እና 300ሺህ ዳቦ የመጋገር አቅም እንደሚኖራቸው የተገለፀ ሲሆን÷ በአስሩም ከተሞች ሰርቶ ለማጠናቀቅ 12 ወራት እንደሚፈጅ ተገልጿል፡፡

ፕሮጀክቱ የከተሞቹን የዳቦ ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ ለ1ሺህ 200 ሰዎች የስራ እድልን እንደሚፈጥርም ነው የታወቀው፡፡

ለአጠቃላይ ፕሮጀክቱ በጀት 800ሚሊየን ብር የተያዘለት ሲሆን÷ ፋብሪካዎቹ ሰመራ፣ ጅግጅጋ፣ ሀረር፣ ነቀምት፣ ጎንደር፣ ደሴ፣ አሶሳ፣ ሀዋሳ፣ ወላይታ ሶዶ እና ቦንጋ ይገነባሉ ነው የተባለው፡፡

በፈቲያ አብደላ