የሀገር ውስጥ ዜና

አዲሱ ዓመት ኢትዮጵያ የድል ብስራት የምትሰማበት ዓመት ይሆናል- ትውልደ ኢትዮጵያውያን

By Alemayehu Geremew

September 10, 2021

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲሱ ዓመት ኢትዮጵያ የመከራ ጊዜዋን አልፋ የድል ብስራት የምትሰማበት ዓመት እንደሚሆን እምነታቸው መሆኑን በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ገለጹ።

ኢትዮጵያ በ2013 ዓ.ም በችግርና በመከራ ውስጥ ያለፈችበት ፈታኝ ጊዜ እንደ ነበር ዳያስፖራዎች ገልጸዋል፡፡

በ2014 ዓ.ም ግን ይህን አስጨናቂ ጊዜ በማለፍ ድሏን የምታረጋግጥበት ዓመት ይሆናል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

ዳያስፖራዎቹ “አዲሱ ዓመት የኢትዮጵያ ጠላቶች አንገታቸውን ይደፋሉ፤ ሕዝቡም በምርጫ የመረጠው አዲስ መንግስት ተመስርቶም አዲስ ስርዓት የሚገነባበት ዓመት ይሆናል” ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ከፍ እንደምትልና፣ ኢትዮጵያውያን እጅ ለእጅ ተያይዘው እንደሚሻገሩ ያላቸውንም እምነት ገልፀዋል።

መጪው የብርሃን ጊዜ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተስፋ ፣በፍቅር ፣በደስታ ፣በመከባበር ፣በመተሳሰብ እና ያላቸውን ለተቸገሩ ወገኖቻቸው በማካፈል መልካምነታቸውን የሚያሳዩበት ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ዳያስፖራው በ2014 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሕዝብ ኑሮ በሚያሻሽሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸውም ኢዜአ ያነጋገራቸው በእንግሊዝና በኖርዌይ ሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ገልጸዋል።