የሀገር ውስጥ ዜና

በቡራዩ ከተማ ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎች ተያዙ

By Alemayehu Geremew

September 10, 2021

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በቡራዩ ከተማ አስተዳደር በሕገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ የጦር መሳሪያ መያዙን የከተማዋ ፖሊስ ገለፀ፡፡

በሕገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የተያዙት 400 ተተኳሽ የብሬን ጥይቶች እና 2 ሺህ 558 ተተኳሽ የክላሽ ጥይቶች፣ እንዲሁም መጠናቸው አነስተኛ እና ከፍተኛ የሆኑ 3 ሺህ 94 ጩቤዎች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የጦር መሳሪያዎቹም ከአማራ ክልል ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከሚሴ ከተማ በአይሱዙ መኪና ተጭነው ለሽብር ዓላማ ሊውሉ ሲንቀሳቀሱ በቡራዩ ከተማ መያዛቸውን ነው የከተማ አስተዳደሩ፣ የአካባቢው ሠላምና መረጋጋት ስራ አስፈፃሚ ኮማንደር አብዱራዛቅ ነጋ የተናገሩት፡፡

ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያው በአካባቢው ማሕበረሰብ ጥቆማ እና በፀጥታ አካላት መያዝ እንደቻለም ነው የኦቢኤን ዘገባ ያመላከተው፡፡