የሀገር ውስጥ ዜና

ሃገርን አደጋ ላይ ለመጣል በሚሰሩ የተራድኦ ድርጅቶች እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ተገለጸ

By Meseret Awoke

September 13, 2021

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)ሃገርን አደጋ ላይ ለመጣል በሚሰሩ አንዳንድ የተራድኦ ድርጅቶች እርምጃዎች እንደሚወስድ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያን ሉዕላዊነት፣ አንድነትና ደህንነት አደጋ ላይ በሚጥሉ ጉዳዮች እንዲሁም ከተቋቋሙበት አላማ ውጪ በሚንቀሰቀሱ አንዳንድ የተራድኦ ድርጅቶች ላይ በቅርቡ የማስተካከያ እርምጃዎችን እንደሚወስድ ነው ኤጀንሲው ያስታወቀው፡፡

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እንደገለፁት÷ የሀገሪቱን ህግና ስርዓት ሳያከብሩ ከተቋቋሙበት አላማ ውጪ በሚንቀሰቀሱ አንዳንድ የተራድኦ ድርጅቶች ላይ በቅርቡ እንደጥፋታቸው መጠን ከማስጠንቃቂያ ጀምሮ እስከማገድና ማፍረስ የሚደርሱ የተለያዩ የማስተካከያ እርምጃዎች ይወሰዳሉ፡፡

“የኢትዮጵያን ሉዕላዊነት፣ አንድነትና ደህንነት አደጋ ላይ በሚጥሉ ጉዳዮች ላይ በሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ ምህረት የለንም፡፡

በእንዲህ አይነት ጉዳይ ላይ የምንደረደርበት ሁኔታ በጭራሽ አይኖርም” ሲሉ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ መግለጻቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡

የተወሰኑ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከሃገር ጥቅም በተፀራሪ በሆነ ጉዳይ ላይ እንደሚንቀሳቀሱ መረጃዎች አሉን ያሉት አቶ ፋሲካው ድርጊቱ የሀገርን ጥቅም የሚጎዳ በመሆኑ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፤ የማጣራቱን ስራ እንደጨረስን አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ የሚወሰድ ይሆናል ብለዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!