የሀገር ውስጥ ዜና

የጦላይ ማሰልጠኛ ያሰለጠናቸውን የሠራዊት አባላት አስመረቀ

By Meseret Demissu

September 14, 2021

አዲስ አበባ ፣መስከረም 4፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ)ጦላይ ባለሌላ ከፍተኛ ማዕረግተኛ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የሀገር ጥሪን ተቀብለው መሰረታዊ ውትድርናቸውን ያጠናቀቁ ሰልጣኞችን አስመርቋል።

ሰልጣኞቹ በመሰረታዊ ውትድርና ማግኘት ያለባቸውን የተግባር እና የንድፈ ሃሳብ ስልጠናዎችን በተገቢው መንገድ አግኝተዋል።

በምረቃ መርሃግብሩ ሜጀር ጀነራል ሃጫሉ ሸለማ፣ የመከላከያ ህብረት ሰው ሃብት ዋና መምሪያ ሃላፊ÷ ብርጋዴል ጄነራል ጦምሲዶ ፊታሞ፣ የትምህርት ቤቱ ዋና አዛዥ እና ሌሎች ከፍተኛ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የትምህርት ቤቱ አዛዥ ብርጋዴል ጄነራል ጦምሲዶ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ሃገሬ ኢትዮጵያን አድናለሁ ብላችሁ ወደ ጦላይ ማሰልጠኛ መጥታችሁ የወታደራዊ ጥበብን ተምራችሁ ለምረቃ በመብቃታችሁ ኮርተንባችኋል ብለዋል።

ሰልጣኞቹ የመሰረታዊ ውትድርና መመዘኛዎችን አሟልታችሁ የተኩስ፣ የአካል ብቃት እና ሌሎችንም የተግባር እንዲሁም የንድፈ ሃሳብ ስልጠናዎችን በብቃት ወስዳችሁ ለዛሬ ቀን ስለበቃችሁ ሃገራችሁ ትኮራባችኋለችም ነው ያሉት።

‘’እኔ እያለሁ ሃገሬ አትደፈርም’’ ብለው ወደተለያዩ የማሰልጠኛ ማዕከላት ገብተው የውትድርና ስልጠናዎችን እየወሰዱ መሆኑንም አንስተዋል።

ዛሬ ለምረቃ ከበቁ ምልምል ወታደሮች ውስጥ የአየር ሃይል እና የኢንጂነሪንግ ዘርፍ እንዲገቡ ተለይተው ስልጠና የተሰጣቸው መሆኑንም አንስተዋል።

ስልጠናው በሌሊት እና በቀንም ጭምር ሲሰጥ የቆየ ሲሆን÷ ምረቃው ለሁለተኛ ዙር የተከናወነ የመሰረታዊ ውትድርና ስልጠና ምረቃ እንደሆነም ተነግሯል።

በይስማው አደራው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!