የሀገር ውስጥ ዜና

በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለሰራተኞች የሚሆን የመኖሪያ ቤት ግንባታ ተጀመረ

By Meseret Awoke

September 14, 2021

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለሰራተኞች መኖሪያ ቤት ግንባታ ማስጀመሪያ መሰረተ ድንጋይ ተቀምጧል።

ኘሮጀክቱ 13 ህንጻዎች ያሉት ሲሆን÷ ለ6ሺህ 500 ሰራተኞች መኖሪያነት የሚያገለግል ነው።

በመድረኩ የተገኙት የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረዳትኘሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ኘሮጀክቱ ለከተማዋ ትልቅ ሀብትና አቅም መሆኑን ገልጸዋል።

ከንቲባው አክለውም ከከተሞች እድገትና ስፋት ጋር ተያይዞም ለነዋሪው ምቹ የመኖሪያ ቤት፣ የትራንስፖርትና ሌሎችንም አገልግሎት ለማቅረብ አስተዳደሩ አቅም በፈቀደ መልኩ ጠንክሮ የሚሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዋና ስራአስኪያጅ አቶ ፍጹም ከተማ በበኩላቸው÷ የመኖሪያ ቤት ኘሮጀክቱ በግቢው መገንባት ለሰራተኞች ከገቢያቸው ጋር የተመጣጣነ አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ ተቋሙን ውጤታማ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

የኮርነርስቶን ዴቨሎኘመንት መስራችና ዋና ስራአስኪያጅ አቶ ሲራክ አምባዬ ኘሮጀክቱ በአንድ አመት ከግማሽ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል።

ከዚህ ኘሮጀክት ስኬትም በመነሳት በሐዋሳ ተጨማሪ የሰራተኞች መኖሪያ ግንባታ የሚኖር ሲሆን÷ ወደ ሌሎች ከተሞችም ለማስፋት እቅድ መኖሩን መግለጻቸውን ከከተማው አስተዳደር ህዝብ ግንኙነት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!