Fana: At a Speed of Life!

 በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ በንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 26 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ የሰጎ እና የሲሌ ወንዝ በመሙላቱ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ በተለያዩ ቀበሌዎች ላይ የንብረት ጉዳት ደረሰ።

በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ትላንት ለሊት የጣለውን ዝናብ  ተከትሎ የሰጎ እና ሲሌ ወንዝ በመሙላቱ ቆላ ሸሌ፣ ቤሌ ንኡስ ፣ሸሌ ሜላ እና ኤልጎ ቀበሌዎች ላይ   የጎርፍ አደጋ  ተከስቷል።

በዚህም  በቀበሌው የሚገኙ አብዛኛው ቤቶች በውሀ ተውጠዋል ፣ የቤት ንብረት ወድሟል ፣በማሣ ላይ ያለ ቋሚ ሰብል እና ንብረት ላይም ጉዳት ደርሷል ነው የተባለው።

በቀበሌዎቹ ሰብአዊ እርዳታ በፍጥነት ለማድረስ እንቅስቃሴ መጀመሩን ከጋሞ ዞን አስተዳደር የህዝብ ግንኙነት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በተያያዘ ዜና በጋሞ ዞን ጋጮ ባባ ወረዳ እየጣለ ባለው ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ በተከሠተ የመሬት ናዳ የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም እየተሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

በአደጋው የሰው ህይወት ከመጥፋቱ ባሻገር 170 ቤተሰቦች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡

ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ነው የተባለው፡፡

ወቅቱን ያልጠበቀው ዝናብ በመቀጠሉ ምክንያት ተመሳሳይ አደጋ ሊደርስ ይችላል ተብሎ በተገመቱ አካባቢዎች የሚኖሩ ወገኖችን የማንሳት ስራ መሠራቱ ተገልጿል፡፡

እንዲሁም በዞኑ ከፍታማ ቦታዎች እና ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ ዞኑ አሳስቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.