የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ በኢኮኖሚ አሻጥር ላይ ሲሳተፉ ነበር የተባሉ የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ

By Meseret Awoke

September 14, 2021

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)በአዲስ አበባ እስካሁን በኢኮኖሚ አሻጥር ላይ ሲሳተፉ የነበሩ 1 ሺህ 967 ንግድ ድርጅቶች ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎች መወሰዱን የከተማው ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡

ቢሮው በየደረጃው ከተዋቀረው የቁጥጥርና ክትትል ልዩ ግብረ-ሃይል ባለፉት ሳምንታት ያከናወናቸውን ተግባራት ገምግሟል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልፈታ የሱፍ÷ የዋጋ ንረቱን ከመቆጣጠር ባለፈ በተወሰነ መልኩም ቢሆን አንዳንድ ምርቶች ላይ የዋጋ ቅናሽ መታየቱና የበዓል ገበያው የተረጋጋ ሆኖ እንዲያልፍ የቁጥጥር ግብረ-ሃይሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

ልዩ ግብረ-ሃይሉ የምርት አቅርቦትና ፍላጎትን በማሳለጥ እንዲሁም የንግድ ህጋዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመረውን ቁጥጥርና ክትትል አጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ አብዱልፈታ አስታውቀዋል፡፡

እስካሁንም ከ31 ሺህ 278 የንግድ ተቋማት መጎብኘታቸውን የገለጹ ሲሆን÷ በ1 ሺህ 967 ንግድ ድርጅቶች ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎች ተወስደዋልም ብለዋል፡፡

በቀጣይም በኢኮኖሚ አሻጥር ላይ በሚሳተፉ ህገወጥ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ኃላፊው መግለጻቸውን ከከተማ አስተዳደሩ ፕረስ ሴክሬታርያት ጽህፈት ቤትያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!