Fana: At a Speed of Life!

በሀዋሳ ከተማ 29 ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ተያዘ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 26 ፣ 2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) በሀዋሳ ከተማ 29 ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ከተሸከርካሪው ጋር መያዙን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ገለፀ፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ ኮለኔል ሮዳሞ ኪአ እንዲሁም የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ኢዮብ አቤቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫው ትላንት ምሽት 5 ሠዓት አካባቢ አይሱዙ ኤፍ.ኤስ.አር ተሸከርካሪ 29 ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ በመኪናው ከፋብሪካ ውጭ በተሰራ በቀላሉ የማይገኝ ሚስጥራዊ ቦታ ተደብቆ ሲጓዝ በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልፀዋል።

ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያውን ሲያጓጉዙ የነበሩት የመኪናው አሽከርካሪ፣ የህገ-ወጥ ጦር መሳሪያው ባለቤት እና የመኪናው ረዳት በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ተገልጿል።

ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር መረጃው ከሳምንት በፊት አስቀድሞ በደረሰ ጥቆማ የታወቀ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፥ ብቃት ያላቸውን የፖሊስ አመራሮች በመመደብ ጉዳዩ በሚስጥር ሲጣራ ቆይቶ ትላንት ምሽት መያዙን ነው የገለፁት።

የጦር መሳሪያው ከየት ተነስቶ ወዴት እንደሚሄድ እና ለምን ዓላማ ሊውል እንደተፈለገ ጭምር መረጃዎች መኖራቸው የተገለፀ ሲሆን፥ ጉዳዩ በምርመራ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ከደቡብ ክልል ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.