Fana: At a Speed of Life!

ቱርክ የኢትዮጵያን “ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” መርህ እንደምትደግፍ ገለፀች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)ቱርክ የኢትዮጵያን “ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” መርህ እንደምትደግፍ በባህሬን ከቱርክ አምባሳደር ገለፁ፡፡
በባህሬን የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት መሪ አምባሳደር ጀማል በከር በባህሬን ከቱርክ አምባሳደር ኢሲን አኪል ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት በሚጠናከርበት ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ አምባሳደር ጀማል የሁለቱ አገራትን የረጅም ጊዜ ግንኙነት አድንቀው ÷የሁለቱ አገራት በአፍሪካ ቀንድ ብሎም በአህጉሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር የኢኮኖሚ ትስስርና ትብብር እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲጠናከር የተጀመረውን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ማጠናከር ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም አምባሳደሩ የኢትዮጵን ወቅታዊና አሁናዊ ሁኔታን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

አምባሳደር ኢሲን በኢትዮጵያ የሚካሄደውን ለውጥ በቅርበት የሚከታተሉ መሆኑን ገልጸው ÷ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ለሌሎችም ተምሳሌት የሚሆን የሰላም፤ የፓለቲካ፤ የኢኮኖሚና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ያለን በመሆኑ በቀጣይ ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም አገራቸው ኢትዮጵያ በተለይም በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የያዘችው አቋም “ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” መር ፓሊሲ እንደምትደግፍ ተናግረዋል፡፡

ይህን በተመለከተ ቱርክ በቂ ተሞክሮ ስላላት ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግና ተሞክሮ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም ሁለቱ ኃላፊዎች የሁለቱ አገራት ታሪካዊና ወንድማማችነታዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ መደረሱን ከባህሬን የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.