“በጠፈር ላይ የተመሰረቱ ቴክኖሎጂዎች እና መተግበሪያዎች ለዘላቂ ልማት”
አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር “በጠፈር ላይ የተመሰረቱ ቴክኖሎጂዎች እና መተግበሪያዎች ለዘላቂ ልማት” በሚል ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ሀገር አቀፍ ጉባኤ አካሄደ።
አቶ አብዲሳ ይልማ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ተቋማቸው ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በስፔስ ዘርፍ ለትብብር ስራ እንደሚተጋ ገልፀው፥ ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ጋር በ2013 ዓ.ም ታህሳስ ወር የተፈራረመው መግባቢያ ስምምነት ትግበራ ማስጀመሪያ መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።
በጠፈር ቴክኖሎጂዎች ላይ ያተኮረው ይህ ጉባኤ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ከመንግስት አካላት ከተውጣጡ ባለድርሻዎች ጋር በመተባበር የተደረገ ነው።
ዶክተር ሙላቱ ዴኣ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት የሳይንስ ባህልን መገንባት ዋና ግብ አድርገው እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።
ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር የተደረሰውን ስምምነት ለመተግበር ወሳኝ የምርምር እና የማኅበረሰብ አገልግሎት መስኮችን በመለየት መፍትሔ አምጪ እንቅስቃሴ ያደርጋል ያሉ ሲሆን የዳሞታ ተራራ ላይ በቅርቡ ፕሮጀክት በመቅረጽ የሳታላይት ተከላ ይደረጋል ብለዋል።
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር መስፍን ቢቢሶ በመድረኩ እንደተናገሩት ዩኒቨርስቲው በዘርፉ በቂ እውቀት የያዙ ባለሙያዎች ለማፍራት ከውጭ ሀገራትም ከውስጥም የዘርፉ ባለሙያዎች በመጋበዝ ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋል።
በጉባኤው የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ አዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ፣ አርባምንጭ፣ ባህርዳር፣ ጂንካ፣ ጅማ እና ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲዎች ተሳትፈዋል።
ከስፔን ማድሪድ ከአውቶኖማ ዩኒቨርሲቲ የመጡት የግብርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ፊሊፔ ዩንታ እና ሌሎች ተመራማሪዎች ጥናታዊ ጽሑፎችን አቅርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።
በመለሰ ታደለ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!