Fana: At a Speed of Life!

ፌስቡክ ፣ ጉግል እና ትዊተር ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ የሚወጡ ሀሰተኛ መረጃዎችን እንደሚያጠፉ አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ጥር 26፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ፌስቡክ ፣ ጉግል እና ትዊተር እየተዛመተ የመጣውን  ኮሮና ቫይረስ  አስመልክቶ የሚወጡ የሐሰት ፈውሶችን እና የተሳሳቱ መረጃዎችን ከገጾቻቸው ላይ እንደሚያጠፉ አስታወቁ፡፡

የቫይረሱ ወረርሽኝ በዓለም ዙሪያ እየተሰራጨ መሆኑን ተከትሎ በቻት ሩም  መስመር ላይ የተሳሳተ መረጃ በፍጥነት እየተስፋፋ መምጣቱ ተገልጿል፡፡

ይህንን ተከትሎ ፌስቡክ በቫይረሱ ዙሪያ የሚወጡትን የሀሰት ፈውሶች እና  ሌሎች ጥንቃቄ የጎደላቸውን ሀሳቦች  ማውረድ እንደሚጀምር ነው ያስታወቀው፡፡

ኩባንያው በዓለም ጤና ድርጅቶች እና በየአካባቢ በሚገኙ ባለስልጣናት ላይ እምነት ባላቸው ሰዎች ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ  የሚችሉ የሐሰት መረጃዎች እንዲሁም የሴራ ይዘት ያላቸው ጽንሰ-ሀሳቦችን  ያስወግዳል ብሏል፡፡

ይህ እርምጃ ከሐሰት ፈውሶች ወይም ከሀሰተኛ የመከላከል ዘዴዎች ጋር የሚዛመዱ እንዲሁም ግራ መጋባትን የሚፈጥሩ መረጃዎችን ያጠቃልላል ነው የተባለው፡፡

በተጨማሪም ኩባንያ በፌስቡክ ላይ ያለውን የማጣራት እና የመቆጣጠር ጥረቶችን በኢንስትግራም ላይም ለመጨመር ማቀዱን አስታወቋል፡፡

የማህበራዊ አውታረመረቡ ትክክለኛ የመረጃ  ምንጮችን ቅድሚያ መስጠት እንደሚፈልግ ገልጾ÷የተመረጡ ድርጅቶች  ስለ ቫይረሱ ለማስተማር የሚረዱ ነፃ ማስታወቂያዎችን እንዲለጥፉ እንደሚፈቅድም አስታውቋል፡፡

እርምጃው በዓለም ዙሪያ በከፍተኛ ደረጃ እየተዛመተ ከመጣው የቫይረስ ስርጭት ጋር ተያይዞ እየመጣ ያለውን የተሳሳተ መረጃ ለመዋጋት ያግዛል ተብሏል፡፡

ከፌስቡክ በተጨማሪም ትዊተር እና ጎግል  ተጠቃሚዎቻቸው በጉዳዩ ላይ የተረጋገጡ ምንጮችን እንዲጎበኙ የማበረታት  ስራ እንደሚጀምሩ ተገልጿል፡፡

ዩቲዩብ በበኩሉ ሰዎች ስለ ቫይረሱ ቪዲዮዎችን ለማግኘት ሲፈልጉ ከታመኑ ምንጮች እንዲያገኙ የማስተዋወቅ ስራ እንደሚያከናውን ተነግሯል ፡፡

ምንጭ፡-ሲ.ኤን.ኤን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.