ቦርዱ የኢህአዴግ ህጋዊ ሰውነት ማጣትን በተመለከተ ውሳኔ ሰጠ
የአዲስ አበባ፣ ጥር 26፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ህጋዊ ሰውነት ማጣትን በተመለከተ ውሳኔ ሰጠ።
ቦርዱ ጉዳዩን አስመልክቶ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ ኢህአዴግ በሊቀመንበሩ በኩል ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በላከው ደብዳቤ ግንባሩ መፍረሱን ለቦርዱ ማሳወቁን ገልጿል።
በሌላ በኩል ደግሞ ህዝባዊ ወያነ ሐርነት ግንባር (ሕወሃት) በሊቀመንበሩ በኩል በተጻፈ ደብዳቤ ግንባሩ በመፍረሱ የንብረት ክፍፍልን አስመልክቶ ቦርዱ ውሳኔ እንዲሰጥበት ጥያቄ ማቅረቡ በመግለጫው ተመላክቷል።
የግንባሩን መፍረስ የመወሰን ስልጣን የቦርዱ በመሆኑ ግንባሩም ሆነ ህወሃት ግንባሩ መፍረሱን መጥቀሳቸው የማይገባ ቢሆንም ቦርዱ ሁለቱ ሊቃነመናብርት ያቀረቧቸውን የጽሁፍ ጥያቄዎ መሰረት በማድረግ ግንባሩ መፍረስ አለበት ወይ? ከፈረሰስ ውጤቱ ምን ይሆናል በሚል ቦርዱ መርምሮ ውሳኔ ሰጥቷል።
ቦርዱ የግንባሩ አባል ሶስት ፓርቲዎች ከግንባሩ ወጥተው አዲስ ውህድ ፓርቲ መመስረታቸውን የብልጽግና ፓርቲን አመሰራረት ከሚያሳየው መዝገብ መረዳቱ ተገልጿል።
በዚህ መሰረትም ግንባሩ በተግባር መፍረሱን ቦርዱ በሙሉ ድምጽ መወሰኑን ነው ያስታወቀው።
የግንባሩን መፍረስ ተከትሎም ቦርዱ የኢህአዴግን ንብረት አስመልክቶ ውሳኔ መስጠት እንደሚያስፈልግ መረዳቱን አብራርቷል።
በመሆኑም የኢህአዴግ አባል ድርጅት የነበሩት ሶስቱ ማለትም አዴፓ ኦዴፓ እና ደኢህዴን ብልጽግና የሚባል ፓርቲ መመስረታቸው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ህወሃት ህልውናውን ጠብቆ የቆየ ፓርቲ በመሆኑ በህጉ መሰረት በብልጽግና እና በህወሃት መካከል የኢህአዴግን ንብረት ክፍፍል ማድረግ እንደሚገባ ቦርዱ ተገንዝቧል።
በዚህ መሰረትም ቦርዱ የኢህአዴግን ንብረት አስመልክቶ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፏል፦
• ብልጽግና እና ህወሃት የኢህአዴግ ንብረትና ሂሳብ የሚያጣራ አጣሪ በጋራ እንዲሰይሙ፣
• በኢህአዴግ ስም ያለ ማናቸውም እዳ ተጣርቶ እንዲከፈል፣
• ከእዳ ክፍያ ቀሪ የሆነ ሃብት 3/4ተኛው ለብልጽግና ፓርቲ ( የሶስቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውህደት በመሆኑ) ¼ተኛ ደግሞ ለህወሃት ድርሻ መሆኑ ታውቆ በዚያ መሰረት ክፍፍል እንዲያጠናቅቁ፣
• ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት በህጉ መሰረት በ6 ወር ውስጥ ለቦርዱ እንዲያሳውቁ ተወስኗል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision