የሀገር ውስጥ ዜና

አርሲ ዩኒቨርሲቲ ለአምባሳደር ሽፈራዉ ጃርሶ የክብር ዶክትሬት ሰጠ

By Tibebu Kebede

September 19, 2021

 

አዲስ አበባ መስከረም 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አርሲ ዩኒቨርሲቲ በዛሬው ዕለት በዋናዉ ካምፓሰ ተማሪዎቹን ሲያስመርቅ ለአምባሳደር ሽፈራዉ ጃርሶ የክብር ዶክትሬት ሰጠ።

ዩኒቨርሲቲዉ ለአምባሳደር ሽፈራዉ ጃርሶ ለሀገራቸው ከባለሙያነት ጀምረዉ እስከ አምባሳደርነት ድረስ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ነው የክብር ዶክትሬት ያበረከተላቸው።

ዩኒቨርሲቲዉ ያስመረቀው በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በሁለተኛና በሶስተኛ ዲግሪ አጠቃላይ 1 ሺህ 924 ተማሪዎችን ነው።

ተመራቂዎቹ በጤና ፣በግብርና አከባቢ ሳይንስ ፣በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ፣ በኮምፒዉቲሽናል እና ተፈጥሮ ሳይንስ እንዲሁም በህግና በሌሎችም የትምህርት ክፍሎች በመደበኛ ፣ በክረምት እና በእረፍት ቀናት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ናቸዉ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ዱጉማ አዱኛ በምርቃት ስነስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር አሁን ያለውን ፈታኝ ሁኔታ ጠቅሰው ተመራቂ ተማሪዎች ችግርን በሚቋቋሙ ተወዳድረው ማሸነፍ የሚችሉ የራሳቸውን የስራ እድልም የሚፈጥሩ እንደሚሆኑ እተማመናለሁ ብለዋል ።

የክብር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ በበኩላቸዉ ÷ በሀገራችን ባለፉት 27 ዓመታት የአንድ ቡድን የባለይነት የተንጸባረቀበት እንደነበር ገልጸዉ በናንተ ጊዜ እንዳይደገም ሰዉን ሁሉ እኩል በማየት ጊዜ ያለፈባቸዉን አመለካከቶችና ድርጊቶች ማስቀረት አለባችሁ በማለት አሳስበዋል።

በተጨማሪም የግብርና ሚንስትሩ ኡመር ሁሴን ፣ የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ እና ፕሮፌሰር እንዳሻው በቀለን ጨምሮ ዩኒቨርሲቲዉ ዛሬ ላለበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ግንባር ቀደም ሚና ለተጫወቱ የዩንቨርሲቲዉ የቦርድ አባላትና ለዞንና ከተማ አስተዳደሮች እዉቅና ሰጥቷል፡፡

ዩኒቨርሲቲዉ በትናንትናዉ ዕለት በቦቆጂ ካምፓስ 831 ተማሪዎችን ማስመረቁ ይታወሳል።

በቅድስት ዘውዱ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!