የፕሬዚዳንት ትራምፕ ንግግር ቅጂ በኮንግረሱ አፈ ጉባኤ መቀደድ እያነጋገረ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ታላቋን አሜሪካ እንመልሳለን ሲሉ ትናንት በዓመቱ የኮንግረሱ የመክፈቻ ንግግራቸው ላይ አንስተዋል።
የትራምፕ ንግግር በአሜሪካ ኮንግረስ በመገኘት የመንግስታቸውን እና የህግ አውጭውን አካል እቅድ የሚጠቁሙበት በየዓመቱ የሚከናወን በፕሬዚዳንቱ የሚደረግ ‘ስቴት ኦፍ ዘ ዩኒየን” ብለው የሚጠሩት ንግግር ነው።
ፕሬዚዳንቱ ንግግራቸውን ከመጀመራቸው በፊት የኮንግረሱን አፈ ጉባኤ እና የዴሞክራቷን ጠንካራ ሰው ናንሲ ፔሎሲ ያቀረቡላቸውን ሰላምታ ሳይቀበሉ መቅረታቸው አነጋጋሪ ሆኗል።
በትራምፕ ድርጊት የተበሳጩት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲም ፕሬዚዳንቱ ንግግራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የንግግሩን ቅጂ ቀደውታል።
አፈ ጉባኤዋ ትራምፕ ባህላዊውን ፕሬዚዳንታዊ አቀባበል ስርዓት ጥሰዋል ሲሉ ወቅሰዋቸዋል።
ፔሎሲ ዶናልድ ትራምፕ ስልጣናቸውን ያለ አግባብ ተጠቅመዋል በሚል ክስ እንዲመሰረትባቸው ቀዳሚውን ሚና መጫወታቸው ይታወሳል።
ፕሬዚዳንቱ 1 ሰዓት ከ18 ደቂቃ በወሰደው ዓመታዊ ንግግራቸው ለቀጣይ አራት አመታት በስልጣን ለመቆየት የሚፈልጉበትን ምክንያት ለኮንግረሱ አቅርበዋል።
በአጭር ጊዜ ውስጥ በማይገመት ፍጥነት ወደፊት ተራምደናል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ ወደ ኋላ አንመለስም ብለዋል።
ትራምፕ ዴሞክራቶችን በተለይም በፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ዋነኛ ተፎካካሪያቸው የሆኑትን በርኒ ሳንደርስን በንግግራቸው ወርፈዋል።
በንግግራቸው ሶሻሊዝም የአሜሪካ የጤና ጥበቃን እንዲያጠፋ አንፈቅድም ሲሉም ተደምጠዋል።
በዚህ የኮንግረስ ዓመታዊ የንግግር ስርዓት ላይ ፕሬዚዳንቱን የሚቃወሙ አንዳንድ አባላት ሳይታደሙ የቀሩ ሲሆን÷ የተወሰኑት ደግሞ ፕሬዚዳንቱ ንግግር በሚያደርጉበት ወቅት አቋርጠው ወጥተዋል።
ምንጭ፡-ቢቢሲ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision