Fana: At a Speed of Life!

የምርምር ተቋማት የእንስሳት ዘርፉን ለማሳደግ ስኬታማ ስራዎችን እያከናወኑ መሆናቸው ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የምርምር ተቋማት የእንስሳት ዘርፉን ለማሳደግ ስኬታማ ስራዎችን እያከናወኑ መሆናቸው ተገለፀ።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ናሚቢያ፣ ኒጀር፣ ሴኔጋልና እንዲሁም የኢትዮጵያ ምርምር ተቋማት ተወካይ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት ስልጠና እየተካሄደ ነው።

ዘመናዊ የዘረመል በሽታዎችን የሚመረምሩ መሳሪያዎችን በመጠቀም በባክቴሪያና በቫይረስ አማካኝነት በእንስሳት ላያ የሚከሰቱ በሽታዎችና እንዲሁም ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች ዙሪያ ከጥር 25 እስከ 29 ቀን 2012 ዓ.ም በሰበታ ከተማ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት ሃብት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ገብረእግዚአብሄር ገብረዮሃንስ በስልጠናው ላይ ባደረጉት ንግግር ÷ የብሄራዊ የእንስሳት ጤና ምርምር ማዕከል በ15 ምርመራዎች ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን ያገኘና በክልሉ ለሚገኙ 14 ላቦራቶሪዎች ድጋፍ ከመስጠት በተጨማሪ ከምስራቅ አፍሪካ ለሚላኩ በሽታዎች የላቦራቶሪ ምርመራ እያካሄደ ይገኛል ብለዋል፡፡

ማዕከሉን የምስራቅ አፍሪካ ዋነኛ ማዕከል ለማድረግና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በራሱ በመፈፀም ስልጠናዎችን እንዲያካሂድና የክትባትና መድሃኒቶችን በማምረት ራሱን እንዲችል እየተሰራ እንደሚገኝም ሚኒስትር ዲኤታው ገልፀዋል።

የብሄራዊ የእንስሳት ጤና ምርመራና ጥናት ማዕከል ዳይሬከተር ዶክተር ተስፋዬ ሩፋኤል በበኩላቸው÷ ማዕከሉ ደስታ በሽታን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ትልቅ ሚና እንደነበረው አስታውሰዋል።

አሁን ላይም የወፎች ጉንፋን፣ አፍታ እግር፣ ፈንግል፣ ተላላፊ የሳንባ በሽታና ለኢቦላ የቅድመ መከላከልና ምርመራ ስራዎችን እያካሄደ እንደሚገኝ መናገራቸውን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.