Fana: At a Speed of Life!

ከተመድ 76ኛ ጉባዔ ጎን ለጎን ኢትዮጵያ ላይ ብዥታ ያለባቸውን ወገኖች ትክክለኛ መረጃ እንዲይዙ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የተመድ 76ኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ኒው ዮርክ የሚገኙት ም/ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከመንግስታት እና ዓለም አቀፍ ደርጅቶች ተወካዮች ጋር ውይይችን እያደረጉ መሆኑን አምባሰደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ፡፡
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው የስልክ ቃለ-መጠይቅ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ አስተያየት የሚሰጡ እና አቋም የሚይዙ ወገኖችን በመለየት በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ እንዲወስኑ ትክክለኛውን መረጃ መስጠት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ስለወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ፣ ስለሰብዓዊ ድጋፍ አሰጣጥ ሂደት፣ ኢትዮጵያ ከተለያዩ ወገኖች ጋር ያላትን የሁለትዮሽ እና የሶስትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ስላላት ፍላጎት፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ በተመለከተ በአንዳንድ ወገኖች ያለው የተሳሳተ ግምት እንዴት መስተካከል እንደሚቻል አቶ ደመቀ ገለጻ ማድረጋቸውን አምባሰደር ዲና ገልጸዋል፡፡
ከዓለም ምግብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር፣ ከተመድ ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽር፣ ከተመድ የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ዋና ዳይሬክተር፣ ከቬንዜዌላ፣ ከአረብ ኤምሬትስ፣ ከጋቦን፣ ከኒጀር፣ ከአየር ላንድ፣ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አቶ ደመቀ መኮንን ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይታቸውም በሰላም እና ጸጥታ ኢትዮጵያ እያደረገች ስላለው ጥረት፣ ሰብዓዊ ድጋፍ እና መብት ጥበቃን በተመለከተ እየተደረገ ስላለው እንቅስቃሴ እና የኢትዮጵያ መንግስት ጥረትን ያልተገነዘቡ ወገኖች እውነታውን እንዲረዱ መረጃዎች የመስጠት ስራ ተሰርቷል ብለዋል፡፡
ይህም ስራ የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት ያጠናክራል ያሉት አምባሰደር ዲና ሙፍቲ በኢትዮጵያ ላይ ያለውን ብዥታ ለማጥራት ያግዛል ብለዋል፡፡
በተለይም በሰብዓዊ ድጋፍ አሰጣጥ፣ በህግ ማስከበር ስራ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያለውን ብዥታ ለማጥራት እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.