በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ከ18 ሺህ 900 በላይ ኢንተርፕራይዞችን አውድሟል
አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል እና የክልል የሥራ ዕድል ፈጠራ አካላት በ2013 ዓ.ም የዕቅድ አፈጻጸምና የተያዘው በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ያተኮረ ውይይት እያደረጉ ነው ።
መድረኩን የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራ ምግብ ዋስትና ኤጄንሲ እና ከፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን ጋር አዘጋጅቶታል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የአማራ ክልል ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ ባደረጉት ንግግር በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ከ5 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ነው ብለዋል።
ሰሜን ወሎ፣ ዋግኽምራ፣ ሰሜን እና ደቡብ ጎንደር ዞኖች በአሸባሪው ትህነግ ቡድን ከፍተኛ የንብረት ውድመት ደርሷል ማለታቸውን የዘገበው አሚኮ ነው።
በአሸባሪውና ወራሪው ቡድን ከ18 ሺህ 900 በላይ ኢንተርፕራይዞች፣ ከ23 በላይ ኮሌጆች፣ ብዙ የላቦራቶሪ እቃዎች እና የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ተቋማት መውደማቸውንም አንስተዋል።
ቀጣዩ የሥራ እድል ፈጠራ እቅዳችንም በአፋርና በአማራ ክልል የወደሙ ተቋማትን መልሶ ማልማት ዋነኛው ሥራ ሊሆን ይገባል ተብሏል።
ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሃብት ያላት መሆኗን በማንሳትም የሥራ ዕድል ፈጠራ እቅዱ ኢኮኖሚን ሊያሳድግ የሚችል መሆን አለበት ነው ያሉት።
ጠንክሮ መሥራት ከተቻለ ሃገሪቱን በአጭር ጊዜ ማሳደግ እንደሚቻልም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ያለውን የሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ በዓመት በትንሹ 3 ሚሊየን የሥራ እድል መፍጠር ተገቢ መሆኑ ተነስቷል።
የሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽንም እስከ 2017 ዓ/ም 14 ሚሊየን የስራ እድሎችን እስከ 2022 ደግሞ 20 ሚሊየን የሥራ እድሎችን ለመፍጠር እየሰራ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።
ኮሚሽኑ በ2014 ዓ/ም 3ነጥብ 1ሚሊየን የሥራ እድሎችን ለመፍጠር ከፌደራልና ከክልል የሥራ ፈጠራ አካላት ጋር እንደሚሰራም ተነግሯል።
በውይይት መድረኩ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽነር ንጉሡ ጥላሁን፣ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሳኒ ረዲ ጨምሮ ከፌዴራልና ከየክልሎች የተውጣጡ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችና የሥራ ዕድል ፈጠራ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ናቸው።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!