በወረራው የወደሙ የጤና ተቋማትን ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ ነው-ዶ/ር ሊያ ታደሰ
አዲስ አበባ፣መስከረም 16፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አማራና በአፋር ክልሎች በወረራው የወደሙ ጤና ተቋማትን ወደ ስራ ለማስገባትና ለተፈናቃይ ወገኖችን የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ከክልል መንግስታት ጋር እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ተናገሩ።
በጤና ሚኒስትሯ የተመራ የልኡካን ቡድን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ህክምናቸውን እየተከታታሉ የሚገኙ የፀጥታ አካላትን ዛሬ ጎብኝተዋል፡፡
ሚኒስትሯ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት የህወሃት የሽብር ቡድን የህዝብ መገልገያ በሆኑ የጤና ተቋማት ላይ በፈጸመው ዝርፊያና ውድመት በሁለቱ ክልሎች የሚገኙ በርካታ የጤና ተቋማት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
የጤና ተቋማቱን እንደ ጉዳት መጠናቸው ልየታ በማድረግ በፌዴራልና በክልል መንግስታት እንዲሁም በዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች ድጋፍ ደረጃ በደረጃ መደበኛ የጤና አገልግሎት የሚሰጡበት ሁኔታ ለማመቻቸት ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።
ከወረራው ነጻ የወጡ አካባቢዎችን የጤና አገልግሎት ለማስቀጠል የመድሃኒትና የህክምና ግብዓቶችን ከማሟላት ጀምሮ ከክልል ጤና ቢሮዎች ጋር በመቀናጀት ለተፈናቃዮች የተሟላ የጤና አገልግሎትን ለማቅረብ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
የልኡካን ቡድኑ በሽብር ቡድኑ ጉዳት የደረሰበትን በሰሜን ጎንደር ዞን የዛሪማ ጤና ጣቢያ ጨምሮ በደባርቅ ከተማ የሚገኙ ተፈናቀይ ወገኖች ያሉበትን ሁኔታ በአካል ተገኝቶ መጎብኘቱንም ዶክተር ሊያ ገልጸዋል።
በክልሉ አራት ዞኖች አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ የጤና ተቋማት በመዘረፋቸውና በመውደማቸው ምክንያተ ከ4 ሚሊዮን ለሚበልጥ ህዝብ የጤና አገልግሎት መስጠት አለመቻሉን የገለፁት ደግሞ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ታሪኩ በላቸው ናቸው።
በዞኖቹ የሽብር ቡድኑ በፈጸመው ወረራ ዝርፊያና ውድመት 25 ሆስፒታሎች 277 ጤና ጣቢያዎች 1ሺ 162 ጤና ኬላዎች
ሙሉ በሙሉ ይሰጡት የነበረውን የህክምና አገልግሎት ማቋረጣቸውን ገልጸዋል፡፡
በጤና ተቋማቱ ተመድበው ይሰሩ የነበሩ ከ7 ሺህ 600 በላይ የጤና ሙያተኞችም ስራ ለማቆም መገደዳቸውን ምክትል ቢሮ ሃለፊው አብራርተዋል።
የጤና ተቋማቱን ዳግም ወደ ስራ ለመመለስ እንዲቻል ኮሚቴ ተቋቁሞ የጉዳት መጠኑ መለየቱንም አስታውቀዋል።
በደቡብ ጎንደር ዞን የሚገኘውን የንፋስ መውጫ ሆስፒታል ስራ ለማስጀመር የሚያስችል የቁሳቁስና የመድሃኒት ግብአት ድጋፍ በማድረግ ለአካባቢው ህብረተሰብ የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና እንዲሰጥ ሁኔታዎች መመቻቱንም ተናግረዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አፀደወይን በበኩለቸው እንደገለጹት የዩኒቨርሲቲው አጠቀላይ ስፔሻለይዝድ ሆስፒታል ህክምናቸውን ለሚከታታሉ የፀጥታ አካላት ተገቢውን የህክምና ድጋፍ እየሰጠ ነው፡፡
ዩኒቨርሲቲው በክልሉ በወረራው ጉዳት ለደረሳባቸው የጤና ተቋማት ማቋቋሚያ የሚውል 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ወጋ ያላቸው መድሃኒቶችና የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉን ፕሬዘዳንቱ ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!