በህብረቱ ከፍተኛ አመራሮች ደረጃ በጾታ እኩልነትና ትምህርት ዙሪያ የሚመክር ጉባኤ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ጥር 27፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ከፍተኛ አመራሮች ደረጃ በጾታ እኩልነትና ትምህርት ዙሪያ የሚመክር ጉባኤ በአዲስ አበባ እተካሄደ ነው።
በጉባኤው የህብረቱ አባል ሃገራት ከፍተኛ አመራሮች ትምህርትን ለሴቶችና ህጻናት ተደራሽ ማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ እየመከሩ ይገኛሉ።
በመድረኩ የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፥ በአህጉሪቱ ያሉ ትምህርት ቤቶችን ከግጭትና ጦርነት ቀጠና ነጻ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በጉባኤው ከ12 ሚሊየን በላይ ህጻናት በአህጉሪቱ በሚፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ርቀው እንደሚገኙ ተመላክቷል።
ከእነዚህ ውስጥም 55 በመቶ የሚሆኑ ሴት ታዳጊዎች መሆናቸው ነው የተገለጸው።
በተለይም ከሰሃራ በታች ባሉ ሃገራት ግጭት በሚነሳባቸው አካባቢዎች 90 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች የትምህርት ቤቶችን በር ረግጠው አያውቁም ነው የተባለው።
በአህጉሪቱ የሚገኙ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች በተገኙበት ምክክር መደረጉን ያደነቁት ፕሬዚዳንት ሳህለወቅርቅ፥ ይህም አፍሪካ በአሁኑ ወቅት የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራች መሆኑን ያሳያል ነው ያሉት።
ከዚህ ባለፈም አፍሪካ በ2020 የጦር መሳሪያ ድምጽ የማይሰማባት አህጉር ትሆን ዘንድ የተያዘውን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ የአባል ሃገራት መንግስታት እየሰሩ ያለው ስራ አበረታች መሆኑን አንስተዋል።
በቆንጂት ዘውዴ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision