Fana: At a Speed of Life!

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የደህንነት ካሜራዎችን ስራ አስጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎችን ደህንነትና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራውን ለማጠናከር የሚያግዙ 158 የደህነት ካሜራዎች መትከሉን አስታወቀ።

የደህንነት ካሜራዎቹ በአራቱም ጊቢዎች በሚገኙ የምግብ አዳራሾች፣ ቤተ መጽሃፍት፣ በተማሪዎች ማደሪያና የመማሪያ ህንጻዎች እንዲሁም በዋና ዋና የመግቢያ በሮች መተከላቸውን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን ገልፀዋል።

ካሜራዎቹ የ24 ሰዓት ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ መረጃዎችን ለማቀበል የሚያስችሉ ናቸውም ተብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም ለደህንነት ስጋት ናቸው ተብለው በተለዩ ቦታዎች ላይ ተጨማሪ የደህንነት ካሜራዎችን ለመትከል የግዢ ጨረታ በመከናወን ላይ መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

በተተከሉት ካሜራዎች ባለፈው ጥቅምት ወር በተማሪዎች ማደሪያ ህንጻ ተከስቶ የነበረው የቃጠሎ አደጋ ፈጻሚዎችን ለመለየትና ለፍርድ ቤት እንደማስረጃ ሆኖ ማገልገል መቻሉንም አስረድተዋል።

ዩኒቨርሲቲው የተማሪዎችን ደህንነት ይበልጥ አስተማማኝ ለማድረግም አንድ ወጥ የኤሌክትሮኒክስ መታወቂያ ካርድ ለማዘጋጀት እንቅስቃሴ ጀምሯል ብለዋል።

የኤሌክትሮኒክስ መታወቂያ ካርዱ በመግቢያ በሮች እና በምግብ መመገቢያ አዳራሽ በሮች ላይ በሚገጠሙ መሳሪያዎች አማካኝነት የተማሪዎችን ማንነት ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ መናገራቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.