Fana: At a Speed of Life!

እስከ ጥቅምት መጨረሻ 1 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል የግብርና ምርቶችን ለማቅረብ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዘንድሮ እስከ ጥቅምት ወር መጨረሻ በህብረት ሥራ ማህበራት በኩል 1 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል የግብርና ምርቶችን ለማህበረሰቡ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን የፌዴራል ህብረት ሥራ ኤጀንሲ ገለጸ።
አሸባሪው ህወሓት የውጊያ ግንባሩን ከጠመንጃ ውጊያ በተጨማሪ በመላው አገሪቱ የኢኮኖሚ አሻጥር በመፍጠር ድምፅ አልባ ጦርነት መክፈቱን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር ገልጸዋል፡፡
በተለይም በከተሞች አካባቢ የአሸባሪውን ቡድን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሚደግፉ ኃይሎች የኑሮ ውድነት እንዲባባስ እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
እነዚህ አካላት ከአሸባሪው ህወሓት ተልእኮ በመቀበል ህብረተሰቡ በኑሮ ውድነት እንዲማረርና በመንግሥት ተስፋ እንዲቆርጥ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
“ይህን ድምፅ አልባ ጦርነት ለማምከን የህብረት ሥራ ዘርፉ ሰፊ ሥራ ሲሰራ ቆይቷል” ያሉት አቶ ኡስማን÷ በዚህም ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
ሁሉንም የሚጎዳውን ይህን ጅምላ ጨራሽ የሆነ የኢኮኖሚ አሻጥር ለመመከት አምራች የህብረት ሥራ ማህበራት የግብርና ምርቶችን አሰባስበው ከኢንዱስትሪና ከሸማች ማህበራት ጋር ቀጥታ የሆነ ትስስር እንዲፈጥሩ መደረጉን ገልጸዋል።
አምራቹ ላመረተው ምርት ፍትሃዊ ዋጋ እንዲያገኝ ሸማቹም የሚፈልገውን ምርት በተመቸው ቦታና ጊዜ በተመጣጣኝ ዋጋና ጥራት እንዲያገኝ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ባለፉት ሁለት ወራት 253 ሺህ ኩንታል ምርት ተዘጋጅቶ ለሸማችና ኢንዱስትሪ ማህበራት እንዲቀርብ መደረጉን ጠቁመው÷ እስከ ጥቅምት ወር መጨረሻ ድረስ ደግሞ 1 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል የግብርና ምርቶችን ለማህበረሰቡ ለማቅረብ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎና የማሽላ ምርቶች የሚቀርቡ መሆኑን ጠቅሰው÷ ከአትክልት ሽንኩርትና ቲማቲም፣ ከቅመማ ቅመም በርበሬ እንዲሁም ከጥራጥሬ ምስር፣ አተር፣ ሽምብራና ባቄላ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በአማራ፣ ሲዳማ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች እንደየአካባቢያቸው ሁኔታ ምርቶቹን ለማቅረብ ተለይተዋል ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባና በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች እነዚህን ምርቶች ለማዳረስ እየተሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
ምርቶች በማህበራት መቅረባቸው የተፈጠረው የዋጋ ንረት ትክክለኛ እንዳልሆነ ህብረተሰቡ እንዲረዳ ያስችላል ብለዋል፡፡
የኢኮኖሚ አሻጥር የመመከት ሥራ ተከታታይነት ያለው ስራ የሚጠይቅ በመሆኑ አሸባሪ ቡድኑ እስኪደመሰስ ድረስ በዘላቂነት እንደሚተገበር አስረድተዋል።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን የከፈተውን ሁሉን አቀፍ ጦርነት ለመመከት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም ጠይቀዋል ሲል ኢኤአ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.