በቻይና በኮሮና ቫይረስ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 563 ደረሰ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 28 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በቻይና በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ500 በላይ መድረሱ ተነገረ።
እስካሁን በቫይረሱ ሳቢያ የሟቾቹ ቁጥር 563 መድረሱን መረጃዎች ያመላክታሉ።
በትናንትናው እለት ብቻ በሁቤይ ግዛት 70 ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም 3 ሺህ አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች ተገኝተዋልም ተብሏል።
ከዚህ ባለፈም በሆንግ ኮንግ እና ፊሊፒንስ ሁለት ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋልም ነው የተባለው።
በጃፓኗ የወደብ ከተማ ዮኮሃማ ደግሞ 10 ተጨማሪ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።
ከዚህ ባለፈም 3 ሺህ 700 ሰዎች ለሁለት ሳምንታ በልዩ ማቆያ ስፍራ እንዲቆዩ ተደርገዋልም ነው የተባለው።
የቫይረሱ ስርጭት አድማሱን እያሰፋ ሲሆን፥ አሁን ላይ ከቻይና ውጭ ከ260 በላይ የቫይረሱ ተጠቂዎች መገኘታቸው እየተነገረ ነው።
ምንጭ፦ ሬውተርስ